በባህር ዳሩ የአመራሮች ስብሰባ የፋኖ መሪዎችን እስከ መስከረም 30 የመያዝ ዕቅድ ስለመዉጣቱ

ሰላም ጤና ይስጥልን በመላው አለም የምትገኙ የተወደዳችሁ የሮሃ ቲቪ ተከታታዮች፣ የመስከረም 23/ 2016 ዓ/ም የምሽት ዜናዎችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።


በባህር ዳሩ የአመራሮች ስብሰባ የፋኖ መሪዎችን እስከ መስከረም 30 የመያዝ ዕቅድ ስለመዉጣቱ 

  

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአማራ ክልል ግፍ የተሞላባቸው ወንጀሎች ተፈፅመዋል ስለማለቱ እንነግራችኋለን  


በአዲስ አበባ  ከተማ የመስሪያ ቦታቸዉን ስለተነጠቁት አካል ጉዳተኞችም የምንላችሁ አለን


በአማራ ክልል በዛሬዉ ዕለትም ዉጊያዎች ቀጥለዋል በሸኖ የተኩስ ልዉዉጥ ተካሂዷል በደላንታም በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ካምፕ ላይ የቦምብ ጥቃት ደርሷል በዝርዝር የያዝነዉ መረጃ አለ

 


በአዲስአበባ ከ244 በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች የመስሪያ ቦታችን በመፍረሱ ለከፋ ችግር ተዳርገናል አሉ


በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ በአምስት የንግድ ማህበራት ተደራጅተው የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ከስድስት ወራት በፊት እንሰራበት የነበረው ቦታ በመፍረሱና “ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል” ቢባልም እስከአሁን፤ ስላልተሰጠን ለከፋ ችግር ተዳርገናል ሲሉ ተናግረዋል።


ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማህበሩ አባል፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙ 244 በላይ ከሚሆኑ አካል ጉዳተኞች መሃል ለአምስት ግለሰቦች ብቻ የሥራ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን፤ እነሱም ቢሆን ሥራ አለመጀመራቸውን ገልጸዋል።


ሌሎች የተቀሩት 239 የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች በሙሉ ከሥራ ዉጪ መሆናቸውን ገልጸው፤ አብዛኛዎቹ ወደ ልመና እንዲሁም ወደተለያዩ ክፍለ አገራት መሄዳቸውን አመላክተዋል።


ክፍለ ከተማው ከዚህ ቀደም ምትክ ቦታ ሊሰጥ እንደነበረ ገልጸው፤ ነገር ግን ቦታው የወንዝ ዳርቻ ከመሆኑ ባሻገር ለአካል ጉዳተኛ አመቺ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ “እኛ የምንጠይቃቸውን ቦታ ሊያመቻቹልን ፍቃደኛ አይደሉም” ሲሉም ተደምጠዋል።


በተጨማሪም ይሰሩበት የነበረው ስፍራ አሁን የመኪና ማቆሚያ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሆኖ መመልከታቸውን  ገልጸዋል።


“ይሄንንም ክፍለ ከተማውን በምንጠይቅበት ሰዓት፤ ደንብ አስከባሪ የተባሉ ኃይሎችን እየላኩ ከቦታው ያስነሷቸዋል የተረሳ ሲመስላቸው ደግሞ ይመለሳሉ፡፡” ሲሉ ገልጸዋል።


በተጨማሪም “ክፍለ ከተማው የኛን ቦታ ለሌሎች ለመስጠት የማደራጀት ሂደት ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡” ብለዋል።



በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ዉጊያዎች መኖራቸዉ ተገለፀ


በአማራ ክልል በዛሬዉ ዕለት በአንዳንድ አካባቢዎች ዉጊያዎች በመካሄድ ላይ  እንደሚገኙ ተሰምቷል።

በደቡብ ወሎ ደላንታ ከወገል ጤና ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፀሀይ መዉጫ አካባቢ በሚገኝ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ካምፕ ላይ ሌሊቱን ተከታታይ የቦምብ ፍንዳታዎች መድረሳቸዉ እና በዚህም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል። ከፍንዳታው በኋላም አምቡላንስ ወደ አካባቢዎቹ ሲመላለስ እንደነበር ተነግሯል።


በተመሳሳይ ወገልጤና ከተማ አቅራቢያ ቻይና ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም ትላንት ከምሽቱ3ሰዐት ጀምሮ ተኩስ እንደነበር እና ጠዋት 11 አካባቢ ተኩሱ ቆሞ የነበረ ቢሆንም እንደገና ከማለዳዉ 3 ሰዐት ጀምሮ ማገርሸቱን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚዉ ቅርብ ርቀት በሚገኙት ደላንታ ፣ ዋድላ እና ጋሸና አካባቢዎች ላይ ሌሊቱን የተኩስ ድምፆች ሲሰሙ እንደነበር ም ተጠቁሟል። በምዕራብ ወሎም አካባቢዎች ላይ  የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንዳለ ተነግሯል።


እንዲሁም በወልዲያ ከተማ በተደጋጋሚ ቦምብ ተጥሎ መገኘቱን ተከትሎ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ፍርሀትን  እያስከተለ እንደሚገኝ አስተያየታቸውን ለሮሃ የሰጡ ነዋሪ ተናግረዋል።



በባህርዳሩ የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ የፋኖ መሪዎችን በ6ቀናት ለመያዝ መታቀዱ ተሰማ 


የህግ የበላይነት እና አንገብጋቢ ጥያቄዎች በሚል መሪ ቃል የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሲያደርጉት የነበረዉ ስብሰባ መቀጠሉ ተሰምቷል።  በክልሉ አስተዳደር እና በፀጥታ ዘርፍ ሀላፊዉ እየተመራ ነዉ በተባለዉ ስብሰባ የተለያዩ ዉሳኔዎች እየተላለፉ እንደሆነም ተነግሯል።


ከእነዚህ መካከልም በ6ቀናት ዉስጥ የፋኖ አመራሮችን በቁጥጥር ስር በማዋል ቀጣይ ስራዎችን ማስቀጠል ዋነኛ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል። በስብሰባው ላይ እስከ መስከረም 30  ዕቅዱን  በማሳካት ክልሉን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አቅጣጫ መቀመጡ እየተነገረ ይገኛል። በዚህም መከላከያ ሰራዊቱ ከትላንት ሌሊት ጀምሮ በክልሉ ጠንካራ የተባለዉን ዘመቻ መጀመሩ ተሰምቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን (ICHREE) ያቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው ከሆነ ስምንቱም የተለመዱ የአደጋ መንስኤዎች እና አብዛኛዎቹ የጭካኔ ወንጀሎች  አሁን በኢትዮጵያ እየተፈፀሙ ይገኛሉ  ሲል ገልጿል።


የኮሚሽኑ አባል የሆኑት ራዲካ ኩማራስዋሚ በበኩላቸው  በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በግልጽ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ ጉዳዩ የብዙዎች እይታ እያገኘ ነው ይህም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

0 Comments

Login to join the discussion