የታህሳስ 8 የምሽት ዜና

  • በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ውግያ ቀጥሏል፣ ፋኖ የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ ነው። 
  • ፋኖ ዘመነ ካሴ የብልፅግና ወታሮች እስከ ታህሳስ ሰላሳ ድረስ እጅቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።  
  • አቶ ታዬ ደንደዓ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ተሰምቷል።
  • ታዋቂው አርቲስ በብልፅግና ታስሯል።
  • የቀይ ባህር ጉዳይ ከባድ ውጥረት ፈጥሯል

  • ፍ/ቤት ያልቀረቡት አቶ ታዬ
    አቶ ታዬ ደንደአ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ተሰማ
    የብልፅግናው መንግስት መፈረካከስና የርስ በርስ መባላት ወስጥ መግባት ማሳያ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ፍ/ቤት አለመቅረባቸውን ባለቤታቸው ተናግረዋል።
    ከሳምንት ገደማ በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ታዬ ደንደአ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
    ወ/ሮ ስንታየሁ ባለቤታቸው በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው አስታውሰው እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን እንዲሁም ጠበቆቻቸውም እንዲያናግሯቸው እንዳልተፈቀደ ተናግረዋል።
    ወ/ሮ ስንታየሁ ባለቤታቸው አቶ ታዬ ደንደአን ለማናገር “በቀን ሦስት ደቂቃ ብቻ” እንደተፈቀደላቸው ጨምረው ይናገራሉ።
    “ብዙ ማናገር አይፈቀድም። ከ3 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ ብቻ እንደምነህ? ሰላም ነህ? ማለት ብቻ ነው የምችለው። እርሱንም በቅጡ ሳልናገር ፖሊሶቹ ዝም እንድል ይነግሩኛል። ገና እኔ ጋር ሳይመጣ ቶሎ ጨርሱ ይላሉ” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
    ወ/ሮ ስንታየሁ ከቤተሰብ መካከል ለመጠየቅ የተፈቀደላቸው ሁለት ሰዎች ብቻ መሆኑን ተናግረው፣ ከዚያ ውጪ ያሉ ግን መጠየቅ አንዳልተፈቀደላቸው ጨምረው አስረድተዋል።
    የአቶ ታየ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት ከነበረበት የመንግሥት ቤት ‘ሙሉ ንብረታቸውን ሳያወጡ እንደታሸገባቸው’ መናገራቸው ይታወሳል።

  • የአማራ ክልል ውሎ
    በቀጠለው የአማራ ክልል ውግያ ፋኖ የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ ነው
    በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ በተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሎ መዋሉን የሮሀ ምንጮች ገልፅዋል።
    በዛሬው ዕለት በደቡብ ወሎ ዞን  በምትገኘው አልብኮ ወረዳ በአንዳነድ ቀበሌወች ፋኖ መግባቱን ሮሀ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች ።
    ከወረዳው በስተ ደቡብ በኩል በምትገኘው ነጢ ቀበሌ ውሎውን ከባድ የሚባል ጦርነት እየተደረገ እንደላ ታውቋል።
    የተኩስ ልውውጡም በወረዳው በሚገኙ የፀጥታ ሀይሎች ከሚኒሻ እና ፓሊሶች ጋር እንደሆነ ነዋሪው ገልጸዋል። በርካታ የመንግስት ታጣቂዎችና ፓሊሶች ሲገደሉ ቀላል የማይባሉት ደግሞ ቆስለው ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መሄዳቸው ተሰምቷል።
    በሌላ በኩል በትላንትናው እለት በደቡብ ጎንደር በደራ ወረዳ አርብ ገበያ አካባቢ ፣ በፋርጣ ወረዳ ፣አገረ ማሪያም ዙሪያ ከፍተኛ ውጊያ ሲደረግባቸው ውሏል።
    የብልፅግና ሠራዊት ሰሞኑን በዕስቴ እና በጋሳይ ሽንፈት ደርሶበት በሽሽት ላይ እያለ ሴቶችን ጨምሮ ንፁሀንን እንደገደለ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል ።
    ውግያው በሌሎች አካባቢዎች ሲቀጥል በደቡብ ጎንደር አብዛኛው ወረዳዎች እንዲሁም በአዊ ዞነን ቴሊሌ አዋሳኝ አካባቢዎችየሉ ፋኖዎች ውጊያ ላይ መሆናቸውን ምንጮች ያስረዳሉ።
    ሌላው ከሰሞኑ ከባድ ውጊያ ሲደረግበት በነበረው በደቡብ ወሎ አምባሰል አካባቢ ጋብ ቢልም በዞኑ ሌሎች ቦታዎች በደላንታ ወረዳ ከወገል ጤና ወጣ ብሎ ወደ ኮንና ጋሸና መገንጠያ ፣ ሚዛን በተባለ ቦታ ላይ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጦርነት ስለመቀስቀሱ ሰምተናል።

  • የዘመነ ቃለ መጠይቅ
    ፋኖ ዘመነ ካሴ አይደለም ፋኖ የአማራ ገበሬም ነቅቶ ተደራጅቷል ሲል ገለጸ
    የአማራ ህዝባዊ ሃይል መሪ አርበኛ ፋኖ ዘመነ ካሴ ከሮሃ ቲቪ የመዓዛ እንግዳ ጋር ባደረገው ቆይታ በአማራ ክልል ድብን ያለ ጦርነት እየተካሄደ ነው ብሏል፡፡
    በዚህ የአማራ ትግልም ገበሬው  የተሻለ የፖለቲካ አረዳድና አደረጃጀት ይዟል ያለው አርበኛ ዘመነ ካሴ ከፋኖ በሚደረግለት የአመራር እገዛም የተሻለ ውጤት እየመጣ ነው ብሏል፡፡
    "ባል ለውጊያ ተራራ ሲወጣ ፣ ሚስት ከኋላ ስንቅ የምታቀብልበት ሁኔታ እንዳለ ተመልክቻለሁ ያለው ዘመነ  ይህ ሁኔታ እንዳስለቀሰውም አንስቷል፡፡
    ድርድርን በሚመለከትም "ህጻናትን ከሚጨፈጭፍ የአጋንንት ስብስብ ጋር አንደራድርም" ሲል አስረግጧል ፋኖ ዘመነ ካሴ፡፡
    አርበኛው ብልፅግና "ፋኖ እጅ ይስጠኝ" በሚል ላቀረበው ጥሪ ምላሽ ሰጥቷል። በምላሹም እስከታህሳስ ሰላሳ በየአካባቢው ያሉ የብልፅግና ተላላኪዎችና የፀጥታ ሃይሎች በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የፋኖ አደረጃጀት እጃቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል።
    ተመልካቾቻችን የአርበኛ ዘመነ ካሴን እና የጋዜጠኛ መዓዛ መሃመድን ልዩ ቆይታ ከሮሃ ቲቪ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ሙሉውን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

  • የታፈነው አርቲስት
    ታዋቂው የኢት ዮጵ እስክስታ ፊትነስ አሰልጣኝ መታፈኑ ተሰማ
    ታዋቂው የኢት-ዮዽ እስክስታ ፊትነስ አሰልጣኝ እና ባለቤት "Ephi Mack" በአገዛዙ የፀጥታ ሃይሎች መታፈኑ ተሰምቷል።
    አርቲስቱ ስራውን አክባሪ እና ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ 5 የማሰልጠኛ  ቅርንጫፎች ከፍቶ ሲሰራ የነበረ መሆኑም ተነግሯል።
    Ephi Mack ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሌለው ቢታወቅም የብልፅግና ስርአት ግን ለእስር ዳርጎታል።
    በዚህ በብልፅግና ስርአት በርካታ ንፁሃን ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ከመገደላቸውም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ በየማጎሪያው እንዲገቡ ተደርገዋል።

  • የቀይ ባህሩ ውጥረት
    ግዙፉ ነዳጅ አምራች ኩባንያ በቀይ ባሕር በኩል ነዳጅ ማመላለስ አቋረጠ
    ግዙፉ ነዳጅ አምራች ቢፒ (ብሪቲሽ ፔትሮሊየም) በደኅንነት ስጋት ምክንያት ነዳጅ የጫኑ መርከቦቹ በቀይ ባሕር በኩል ለተወሰነ ጊዜ ማለፋቸውን እንደሚያቆሙ አስታውቋል።
    ኩባንያው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ በቀይ ሕር የሚያደርጉት ጉዞን ለማቋረጥ የወሰነው በቅርቡ በሁቲ አማጽያን መርከቦች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነው።
    ይህን ውሳኔ በጊዜያዊነት ያስተላለፈው በአካባቢው ያለው “የደኅንት ሁኔታ አስጊ ስለሆነ ነው” ሲል አብራርቷል።
    በየመን በሁቲ አማጺያን ዒላማ መሆናቸውን ተከትሎ ሌሎች ዓለም አቀፍ የባሕር ጭነት አመላላሽ ድርጅቶች መርከቦቻቸው በቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።
    ከግዙፍ የመርከብ ጭነት አጓጓዦች መካከል አንዱ የሆነው ተቋም የእስራኤልን ካርጎ በቀይ ባሕር በኩል ማስተላለፍ ማቋረጡን አስታውቋል።
    ኤቨር ላየን የተባለው ተቋም መርከቦች “ተጨማሪ ትዕዛዝ እስከሚተላለፍ ድረስ” ጉዞ እንዲያቋርጡ መወሰኑን ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።
    ለነዳጅ እና ጋዝ እንዲሁም ቁሳቁስ ዝውውር የቀይ ባሕር መስመር ከሚመረጡ መንገዶች ዋነኛው ነው።
    በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን ባብ አል-ማንዳብ ወይም 'ጌት ኦፍ ቲርስ' በሚባለውን እና 32 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚሆነው መተላለፊያ ሰርጥ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።
    አማጽያኑ ሐማስን እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን፣ ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦችን በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና በሚሳኤል ዒላማ እንዳደረጉም አስታውቀዋል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

0 Comments

Login to join the discussion