የታህሳስ 11 የምሽት ዜና

  • በፈርስ ቤት ከተማ በሶስቱም አቅጣጫ ከባድ የተባለ ትንቅንቅ እየተካሄደ ለአራተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
  • ፋኖ በጎጃምና በጎንደር የአገዛዙ ሰራዊት ላይ አስከሬን መሰብሰብ እስኪያቅተው ከባድ ምት ማሳረፉ ተሰምቷል፡፡ 
  • እነአዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የመንግስት ሰራተኞች ‹ብሔር› እንዲሞሉ የሚያስገድድ ፎርም ማዘጋጀታቸው ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
  •  ብልጽግና የአዲስ አበባ ት/ቤቶችን ኦሮምኛ አላስተማራችሁም በሚል እየዘጋ መሆኑ ተነግሯል፡፡ 
  • ኤርትራ ወታደሮቿን ከትግራይ እንድታስወጣ ከአዉሮጳ ህብረት የቀረበን ጥሪን ዉድቅ አድርጋለች፡፡ 
  • ብልጽግና በፋኖ የሚደርስበትን ሽንፈት ተከትሎ ንጹኃን ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተዓማኒ መረጃ ማግኘቷን ደግሞ አሜሪካ ገልጻለች፡፡

  • አሜሪካ ለዐቢይ ማስጠንቀቂያ
     ብልጽግና በፋኖ የሚደርስበትን ሽንፈት ተከትሎ ንጹኃን ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተዓማኒ መረጃ ማግኘቷን አሜሪካ ገለጸች
    በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የሚከተለውን ፖሊስ አስመልክቶ፣ የምስክርነት ቃል አዳምጧል።
    በምክርቤቱ ተገኝተው ቃላቸውን የሰጡት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስኤድ/ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳደር ታይለር ቤክልማን ሲሆኑ በኢትዮጵያ በሚታየው የፖለቲካ፣ የደህነንት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አሜሪካ ያላትን አቋም አብራርተዋል።
    ማይክ ሐመር አያይዘው በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭትም የአሜሪካን አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው አመልክተዋል።
    ‹‹ከግጭቱ ጋር የተያያዘ መጠነ ሰፊ እና ከባድ ፆታዊ ጥቃት፣ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ሰው ህይወት መጥፋት እና ከፍተኛ መጠን ያለው የኢኮኖሚ መቃወስን ጨምሮ፣ ከፍተኛ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች አሉ።›› ብለዋል ሀመር፡፡
    ከሳምንታት በፊት ከእነጋዜጠኛ መዓዛ ሙሀመድና ሌሎች የአማራ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገው የነበሩት ማይክ ሀመር በሪፖርታቸው ላይ በአማራ ክልል በአስቸኳይ አዋጁ ስር እየተፈፀሙ ያሉ የንፁሃን ሰዎች ሞት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር፣ እና በዘፈቀደ የሚፈፀም ግድያ ያሳስበኛል ብለዋል፡፡
    አምባሳደሩ ለአሜሪካው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዐቢይ አህመድንና የብልጽግናን አምባገነናዊና አሳፋሪ ተግባራት በተለይም በአማራ ክልል በንጹኃን ላይ የሚፈጽመውን ጭፍጨፋ አጋልጠዋል፡፡
    አምባሳደር ሐመር ብልጽግና በአማራ ክልል ላይ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሳ፣ ኢንተርኔት እንዲለቀቅ እና መገናኛ ብዙሃን ወደ ክልሉ ገብተው ያለውን ሁኔታ እንዲያጣሩ እንዲፈቀድ ለዐቢይ ማሳሰባቸውንም ተናግረዋል፡፡
    የምስክርነቱን ሂደት የመሩት ሊቀመንበሩ ጄምስ፣ አብይ አህመድ፣ ለኢትዮጵያ የባህር በር መኖር አስፈላጊነትን አስመልክተው በቅርቡ አድርገውት የነበረው ንግግር ወደፊት በቀጠናው አዲስ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ፍራቻቸውን ገልፀዋል።
    ማይክ ሐመር ለዚህ ፍራቻ አዘል ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፣ ስጋቱ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የሌሎች በቀጠናው የሚገኙ ሀገራትም ጭምር መሆኑን በማስመር ሲሆን፣ ዐቢይ ለዚህ ንግግራቸው ማስተባበያ መስጠታቸውንም ጠቅሰዋል።

  • የጎጃሙና የጎንደሩ ትንቅንቅ
    ፋኖ በጎጃምና በጎንደር የአገዛዙ ሰራዊት ላይ አስከሬን መሰብሰብ እስኪያቅተው ከባድ ምት ማሳረፉ ተሰማ
    በምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት አካባቢ በፋኖና እና በአገዛዙ ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ከባድ ውጊያ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
    ብልጽግና በርካታ ወታደሮቹን  ወደ ደጋ ዳሞት ሲያስገባ ያረፈደ ቢሆንም በጎጃም እዝ ፋኖ የሚደርስበት ዱላ ግን ከባድ መሆኑ ታውቋል፡፡
    በፈርስ ቤት ከተማ በሶስቱም አቅጣጫ ከባድ የተባለ ትንቅንቅ እየተካሄደ ለአራተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ፣ አገዛዙ ወደ ስፍራው የሚያስገባው ጦርም ሙትና ቁስለኛ ሆኗል፡፡
    ከዚህም ባለፈ ከተማዋን መልሶ ለመያዝ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ሲሆን ፣ ከባህርዳር ፣ ከፍኖተሰላምና ከሌሎች አካባቢዎች በርካታ ሃይል እያስገባ ነው፡፡
    በተጨማሪም ከትናንት ማምሻውን ጀምሮ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ድሮን እየተኮሰ ሲሆን ፣ በዚህም በርካታ ንጹሃንን ጨፍጭፏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎችም ከአራት ጊዜ በላይ ድሮን ተኩሶ ንጹሃንን ገድሏል፡፡ የፋኖ ሃይሎች ግን የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ቀጥለዋል፡፡
    በሌላ በኩል በዚሁ በምዕራብ ጎጃም ከደምበጫ ወደ ፈረስ ቤት በሚወስደው መንገድ የጨረቃ ከሚባለው ቦታ አቅራቢያ የደፈጣ ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ የአገዛዙ ሰራዊት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡
    በምስራቅ ጎጃም መቀመጫ ደብረማርቆስ ከተማ ቦሌ በተባለውና ተደጋጋሚ ውጊያ በሚካሄድበት አካባቢ ትናንት የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ታውቋል፡፡
    በቦሌ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ፋኖ የሚሊሻና የአድማ ብተና አባላቶችን ይዞ እንደወጣም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
    በደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ እየሱሱ ከተማ ትናንት ምሽት በፓትሮል ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የብልጽግና ሰራዊት አባላት ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል፡፡
    በፋኖ የደፈጣ ጥቃት የደረሰበት የአገዛዙ ሰራዊትም ዲሽቃና የመሳሰሉ ከባድ መሳሪያዎችን በህዝቡ ላይ ሲተኩሱ ነበር ተብሏል፡፡
    ፋኖም በዚህ የደፈጣ ውጊያ ፋኖ አራት የብልጽግና ወታደሮችን ይዞ የሄደ ሲሆን ሁለቱም አዛዥ መኮንኖች ናቸው፡፡
    በዚሁ በደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ በፋኖ እና በብልጽግና ታጣቂዎች መካከል ትናንት ለሰዓታት የቆየ ውጊያ ሲካሄድ ነበር፡፡
    በደቡብ ጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ውጊያ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የአገዛዙ ሰራዊት አስከሬን ማንሳት እስኪያቅተው ተመትቷል ይላሉ የፋኖ አመራሮችና አባላት፡፡
    በተጨማሪም መንገዶች ሁሉ ተዘግተውበታል ይላሉ አመራሮቹ፡፡


  • የአማራ ጠሉ ብልጽግና ዕቅድ
     እናት ፓርቲ እነአዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የመንግስት ሰራተኞች ‹ብሔር› እንዲሞሉ የሚያስገድድ ፎርም ማዘጋጀታቸውን ተቃወመ
    ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ለመንግሥት ሠራተኞች እየተሰጠ የሚገኘው ፈተና እንዲሁም ፈተናውን ተከትሎ እየተደረገ የሚገኘው የሠራተኞች ምደባ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል›› ሲል እናት ፓርቲ መግለጫ አውጥቷል፡፡
    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "የመንግሥት ሠራተኞችን ፈተና ፈትኜ ምደባ አደርጋለሁ" እያለ የሚገኝበት ሁኔታ ሲቪል ሰርቪሱን ይበለጥ ውጤታማ ለማድረግ ተፈልጎ ሳይሆን በፖለቲካዊ ውሳኔ የመጣ በመሆኑ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው መግለጫው ጠቅሷል።
    ‹‹መንግሥት እያደረገ የሚገኘው የፈተና እሩጫ የማይፈልጋቸውን ሠራተኞች ለማስወገድ በአንጻሩ ደግሞ የሚፈልጋቸውን ለመተካት ሆን ብሎ ያቀናበረው ስልት መሆኑን ለመገመት አያዳግትም።›› ብሏል ፓርቲው፡፡
    የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንንም መንግሥት በተመሳሳይ መልኩ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ፈተና እየፈተነ መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጠናል ያለው እናት ፓርቲ የፈተናውን መልስ በክፍያ የሚያሰራጩ ግለሰቦች አጋጣሚውን እንደ ገንዘብ ማግኛ ምንጭ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሚገኙም ገልጧል።
    በተጨማሪም ከፈተናው በፊት መልሱ በየትምህርት ቤቱ አስቀድሞ ተለጥፎ መገኘቱንም ከመረጃ ምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል ያለው ፓርቲው ይህን ተከትሎም ፈተናው ለጊዜው መቋረጡንም ደርሰንበታል ሲል አክሏል።
    ‹‹በዚህ ያህል መጠን በተዝረከረከና ለከት ባጣ ሁኔታ ሠራተኛውን "ፈተና ትፈተናለህ" ብሎ ማዋከብ ድብቅ አጀንዳ ከሌለው በስተቀር አንዳች ረብ የለውም።›› ብሏል፡፡
    የሆነው ሆኖ እናት ፓርቲ የሠራተኞች ፈተና አሰጣጥ መንገዱ ሕጋዊ ባለመሆኑ፣ የግልጽነት ችግር ስላለበት እና በፖለቲካዊ ውሳኔ የመጣ ጉዳይ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ እንደሚያምን ገልጧል።
    ‹‹በተለይ ብሔር መጥቀስን መሠረት ያደረጉ ፎርሞች በአዲስ አበባ የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በሰው ሀብት የሥራ ክፍል አማካይነት አስገዳጅ በሆነ መንገድ እንዲሞሉ እየተሠራ መሆኑንም ፓርቲያችን ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ መንግሥት እየሄደበት ያለውን አካሄድ ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል›› ሲል አካሄዱን ኮንኗል።

  • ኤርትራ ስለኢትዮጵያና ወታደሮቿ
    ኤርትራ ወታደሮቹን ከትግራይ እንዲያስወጣ ከአዉሮጳ ህብረት የቀረበ ጥሪን ዉድቅ አደረገች
    የኤርትራ መንግስት የአዉሮጳ ህብረት ፓርላማ ኃይሎቹን ከኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እንዲያስወጣ ያቀረበውን ጥሪ "የፈጠራ ሀሰት ክስ" ሲል ውድቅ አደርጓል።
    ይህ የተገለፀዉ የኤርትራ ማስታወቅያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ትናንት ታህሳስ 20 ቀን 2016 ዓም በቲውተር ይፋ ባደረጉት ጽሑፍ ነዉ።
    የማነ እንደገለፁት "በአሁኑ ጊዜ፣ አንድ የአዉሮጳ ህብረት የፓርላማ አባል የኢትዮጵያ ትግራይ ክልልን ጉብኝት ካደረገ በኋላ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት  አካባቢው ላይ አለ ብሎ የሃሰት ክስ መመስረት የተለመደ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
    የትግራይ ክልል የቴሌቭዥን አገልግሎት አንድ የአዉሮጳ ህብረት ፓርላማ ቡድን ትግራይ ክልልን ጎብኝቶ የኤርትራ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲወጡ ጥሪ ማቅረቡን ዘግቦ ነበር።
    የኤርትራ ጦር ሰራዊት ወደ ትግራይ የገባዉ ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጋር በመሆን በትግራይ ትግራይ በተደረገዉ ጦርነት መሆኑ ይታወሳል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች ከክልሌ ይዉጡ ሲል እየወተወተ መሆኑ ይታወቃል።

  • የዩክሬን ጥሪ ለወንድ ዜጎቿ
    ከአገር ውጭ ያሉ ዩክሬናውያን ወንዶች የአገሪቱን ጦር እንዲቀላቀሉ ጥሪ ሊቀርብላቸው ነው
    ይህ ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ዩክሬናውያን ጥሪ ሊቀርብ የመሆኑ ዜና የተሰማው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱ ጦር አመራሮች ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ የሠራዊት አባላት እንዲመለመሉ ጥያቄ ማቅረባቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።
    በኪዬቭ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንቱ ሁለት ዓመት ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት እየመሩ ካሉ ጦር አዛዦች “ከ450 እስከ 500 ሺህ ሰዎችን” እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል።
    ዜሌንስኪ ተጨማሪ 500 ሺህ ወታደሮችን የመመልመል ጥያቄ ከማጽደቃቸው በፊት ተጨማሪ መረጃ እንዲቀርብላቸው ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
    በዩክሬን የተጨማሪ ወታደሮች መልመላን የተመለከቱ ሪፖርቶች በስፋት መሰማት የጀመሩት አገሪቱ በሩሲያ ጦር ላይ ጀምራው የነበረው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ውጤማ ሳይሆን ከቀረ በኋላ ነው።
    ከዚህ በተጨማሪም ከሩሲያ የተቃጣባትን ወረራ ለመቀልበስ በአውሮፓ እና አሜሪካ እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ሆና የቆየችው ዩክሬን ከምዕራባውያን የምትቀበለው እርዳታ መዘግየት አጋጥሞታል።
    ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዩክሬን ከአሜሪካ ልታገኘ የነበረው የ60 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ በሪፐብሊካኖች አማካይነት በኮንግረሱ ውድቅ ተደርጓል።
    ከአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ሊሰጣት የነበረው የ50 ቢሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁ በሃንጋሪ ምክንያት ታግዷል።
    በአሁኑ ወቅት የተተኳሽ እጥረት እንዳጋጠማት እየተዘገበ የምትገኘው ዩክሬን፤ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ ነዋሪ የሆኑ ዩክሬናውያንን በጦር ሜዳ የማሰለፍ ዕቅድ አላት።
    የአውሮፓ ኅብረት የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሆነው ዩሮስታት አሃዝ እንደሚያሳየው የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ከ18 እስከ 64 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 768ሺህ ወንዶች ከዩክሬን ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ተሰደዋል።
    የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ ቢልድ እና ፖሊቲኮ ከተባሉ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩክሬናውያኑ ወደ አገር ተመልሰው የሚዋጉት “ለክብር” ሲሉ እንጂ “ቅጣትን ፈርተው” አይሆንም ብለዋል።

0 Comments

Login to join the discussion