የታህሳስ 12 የረፋድ ዜና

  • ግብጽ ካሁን በኋላ በአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር አልደራደርም ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
  • የብልጽግናው መንግስት የሚኩራራበት የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ መዘዝ እንዳለው ጥናት አመልክቷል፡፡ 
  • በደጋ ዳሞት ፈረስ ቤት ፣ በደምበጫና በአማኑኤል ከባድ ትንቅንቅ እየተካሄደ ነው፡፡ 
  • እስራኤል ጦርነቱ ካልቆመ በጭራሽ ታጋቾችን አልለቅም ብላለች፡፡



  • የደጋ ዳሞቱ ሽንፈትና ድሮን
    በደጋ ዳሞት ከባድ ሽንፈት ያስተናገደው ብልፅግና ንፁሃንን በድሮን እየጨፈጨፈ ነው
    በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማና ምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማ እየተካሄዱ ያሉ ውግያዎች ቀጥለዋል።
    በአካባቢዎቹ የጎጃም ፋኖዎች ታላቅ ድልና ታሪክ እየፃፉ ነው።
    "እጅ ስጡኝ" ባዩን ብልፅግናንም እጅ እግሩን እያሳጡት መሆኑን ከአካባቢዎቹ የሚወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
    በተለይ በምእራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤትና አካባቢው ላይ እየተደረገ ባለው ውግያ ፋኖን መርታት ያቃተው የብልፅግና ሃይል በንፁሃን ላይ ድሮን እያዘነበ ፣ ከባድ መሳሪያ እየጣለ ነው።
    የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪዎች ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በነበረው ውጊያ የአገዛዙ ጦር ድሮንን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል ነው ያሉት።
    ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ ከ11 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ጠጠር ድንጋይ፣ ድኩል ቃና እና ዝቋላ በሚባለው አካባቢ ውጊያ እንደነበርና ሰዎች መቁሰላቸውንና መሞታቸውን ተናግረዋል።
    ነዋሪዎቹ በተለይ ጠጠር ድንጋይ በሚባለው የከተማው ክፍል ውጊያው እጅግ ከበድ ያለ እንደነበርና አሁንም እንደቀጠለ ተናግረዋል።
    የደጋ ዳሞቷ ፈረስ ቤት ከተማና አብዛኛው ደጋዳሞት በፋኖ ቁጥጥር ስር መሆናቸው ታውቋል።
    ይህን ሽንፈት መቋቋም ያቃተው ብልፅግናም በንፁሃን ላይ ድሮንና ከባድ መሳሪያ እየተኮሰ ህፃን ካዋቂ ሳይለይ እየፈጀ ነው።
    በዚሁ ምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ አቅራቢያ በምትገኘው የጨረቃ ከተማም ከባድ ውግያ እየተካሄደ ነው።
    በዚህም ከደምበጫ ተነስቶ ወደ ጨረቃ ለድጋፍ ያመራው የብልፅግና ሃይል ደፋር ወንዝ የተባለ አካባቢ ላይ እንዲሁም ከደምበጫ ተነስቶ ወደ ደጋዳሞት ፈረስ ቤት ሲያመራ የነበረውን የአገዛዙ ጦር አንጀኔ ላይ የደምበጫ ፋኖዎች በደፈጣ ጥቃት ደምስሰውታል።
    በተመሳሳይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ አማኑኤል  ከተማና አካባቢው ውጊያው ከትናንት በስቲያ መጀመሩንና እስካሁንም እንደቀጠለ ነዋሪዎች ይገልፃሉ።
    በተለይም በተለምዶ «የነጪ» እና «የውሻ ጥርስ» በሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር አመልክተዋል። ነዋሪዎች "ከትናንት በስቲያ 12 ሰዓት ጠዋት የነጪ በሚባለው አካባቢ ውጊያ ተጀመረ፣ እስከ ቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ ውጊያው ቀጥሏል። ጥቂት ውጊያው በረድ እንዳለ ፋኖ  ከተማ ውስጥ ገባ፣ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠራት። በተለምዶ ውሻ ጥርስ በሚባለው አካባቢ መከላከያ ከባድ መሳሪያ መተኮስ ጀምሮ ነበር፣ የጉዳት መጠኑን አሁን ማወቅ አይቻልም፣ ተኩስ አሁንም የነጪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አለ፣ በውሻ ጥርስ በኩል ያለው ግን በርዷል" ይላሉ።
    በዚህ በአማኑኤሉ ውግያ የብልፅግና ወታደሮች ዙ 23ን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ጥለው እየሸሹ መሆኑም ታውቋል።እንዲሁም ወደ አማኑኤል እገባለሁ ያለው የአገዛዙ ጦር ከባድ ሽንፈት አስተናግዶ ወደ ደብረማርቆስ ተመልሷለል።


  • የህዳሴው ግድብና ግብፅ
    ግብፅ ካሁን በኋላ በአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር አልደራደርም ማለቷ ተሰማ
    አምባሰደር ስለሺ በቀለ ግብጽ ከአሁን በኋላ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደማትደራደር ማስታወቋን ተናግረዋል።
    ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከታኅሳስ 7 ቀን እስከ ታኅሳስ ዘጠኝ ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ ያካሄዱት 4ተኛዙር ድርድር ያለ ውጤት ማብቃቱን ብጽና ኢትዮጵያ አስታውቀዋል።
    ድርድሩ ያለውጤት ያበቃው የውኃ አለቃቀን በሚመለከተው ስድስተኛው አንቀጽ ላይ ከግብጽ ጋር መስማማት ባለመቻሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።
    ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው «ግብጾች የሚፈልጉት የውኃ ባለቤትነታችንን ፈርሙልን እና የናንተ ውኃ አጠቃቀም በኛ መልካም ፈቃድ መሆን አለበት የሚል የቆየ ይዘት አለው።በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ውኃው የጋራችን ነው። ፍትኃዊና ርእታዊ በሆነ መንገድ ውሀችንን በጋራ የምንጠቀምበትን ስርዓት ማበጀት አለብን እንጂ ውሀ የናንተ መሆኑን የምንፈርምበት አስፈላጊነትም የለውም ፤ተገቢም አይደለም ፤ነገሩም አያስኬድም በብሔራዊ ጥቅማችን አንጻር ሲባል ነው የተኖረው»ይላሉ።
    የውኃ ሀብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቂ አህመድ ነጋሽ በዚህ ጉዳይ አስገዳጅነት ውስጥ መግባት አይቻልም ሲሉ ሃሳቡን ተቃውመዋል።
    አምባሰደር ስለሺ ግብጽ ከአሁን በኋላ እንደማትደራደር ማስታወቋን ተናግረዋል ።እርሳቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ አቋም ግን «ከመደራደር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም» የሚል ነው። የህዳሴ ግድብ ድርድርና የኢትዮጵያ ፍላጎትበተለይ ግብጽ በድርድሩ ተጠቃሚ ናት ያሉት አቶ ፈቂ አህመድ ብቸኛ አማራጭ ድርድር ስለሆነ መቀጠል አለበት ሲሉ መክረዋል።

  • ብሪክስና ኢትዮጵያ
    ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ከባድ የኢኮኖሚ ችግሮች እንደሚገጥሟት ጥናት አመለከተ
    ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏን ተከለትሎ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ማህበር በተሰራ አንድ ጥናት ላይ የተሳተፉ የምጣኔ ሃብት ባልሙያዎች አገሪቱ አዳዲስ ብድሮችን ልትከለከል ወይም ሊቀነስባት ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
    ከሚጠበቁ ተጽዕኖዎች ውስጥ ለመርሃ ግብሮች የሚለቀቅ ገንዘብ ላይ እክል፣ የመገበያያ ገንዘብ ብር የመግዛት አቅሙ እንዲዳከም ጫና ማድረግ፣ በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ጫና እንደሚፈጥር መጠቆማቸውን የጥናቱ መሪ ዶ/ር ደግዬ ጎሹ ተናግረዋል።
    ከውጫዊ ተጽዕኖዎች ባለፈም ውስጣዊ ተጽዕኖዎች እንዳሉም ባለሞያዎቹ አመልክተዋል።
    ከዚህም ውስጥ በጥምረቱ ላይ የሚደርስ የምዕራባዊያን ጫና፣ የብሪክስ በተለይም የልማት ባንኩ አቅም የሚገኝበት ሲሆን የ11ዱም የብሪክስ አባል አገራት የጥቅም ግጭትም የሚጠበቅ ነው ሲሉ ለአብነት ግብጽና ኢትዮጵያን ያነሳሉ።
    ኢትዮጵያ ከምዕራባውያንና በእነሱ ይዘወራሉ ከሚባሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ተደጋጋፊ መሆኑ፣ እንዲሁም በአቅም አለመፈርጠሟ የብሪክስ ተጠቃሚነቷን እንደሚገድበው ተመራማሪው ተናግረዋል።
    “በአጭር ጊዜ ውስጥ ከብሪክስ ከፍተኛ ጥቅም ወይም ሙሉ ለሙሉ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ልንወጣ የምንችልበት እድል በእኛ አቅም ምክንያት የለም” ብለዋል።
    ዶ/ር ደግዬ፣ ብሪክስ ከተመሰረተባቸው ሰባት ዓላማዎች ውስጥ እንደ ዓለም አቀፍ ንግድ ያሉ ጥቅሞችን ለማግኘት የኢትዮጵያ የቤት ስራ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
    በዋናነትም የብሔራዊ ባንክን አቅምና ገለልተኝነትም ያነሳሉ።
    "ንግድ ወይም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ከተባለ እነሱ እኛ ጋር መጥተው በደንብ ሊሰሩ የሚችሉበት እድል መኖር አለበት። የንግድ ስርዓቱ በጣም የተሻለ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ የገንዘብ ስርዓት፣ የገንዘብ ገበያ እድገት፣ አስተዳደሩ የመሳሰሉት በሙሉ ከብሪክስ አባላት ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። ለዚህ ብቁ የሚያደርጉን ብዙ የቤት ስራዎች አሉብን” በማለት አገሪቱ ዝግጁ እንድትሆን ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ።
    በመሆኑም የአገሪቱ ጥቅም “ሁኔታዎች” ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ ጠቁመዋል።
    “ኢትዮጵያ ከብሪክስ የማትጠቀም ከሆነ በአብዛኛው ሊሆን የሚችለው በራሳችን ችግር ነው” በማለት የሚጎድሉ የቤት ስራዎችን ያነሳሉ።
    እነዚህ ሁሉ ችግሮች ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ የሚመጡ ሆነው ሳለ፣ ከጦርነትና ግጭት ውጪ ይህን ሰራሁ የሚለው የሌለው ብልጽግና ግን ብሪክስን በመቀላቀሉ ታላቅ ጀብዱ አድርጎ እያራገበው ይገኛል፡፡

  • የሃማስ ማስጠንቀቂያ
    ሐማስ "ጦርነቱ ካልቆመ የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ አይኖርም" አለ
    የጋዛ ሰርጥን የሚቆጣጠረው ሐማስ፤ እስራኤል እየፈጸመች ያለውን “ጥቃቷን ካላቆመች” በቀር ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታውቋል።
    እስራኤል እንደምትለው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተገባው የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነት ከተጣሰ በኋላ 2 ሺህ ያህል የሐማስ ወታደሮችን ገድላለች። በተኩስ አቁም ፋታው100 ያክል ታጋቾችን መለቀቃቸው ይታወሳል።
    መስከረም መጨረሻ በሐማስ ታግተው ከተወሰዱ ሰዎች መካከል 120 ያህሉ አሁንም በሐማስ ቁጥጥር እንዳሉ ይገመታል።
    የተባበሩት መንግሥታት ጦርነቱ እንዲቆም የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለ ነው።
    አሜሪካ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያረቀቀው የመፍትሔ ሐሳብ እንዳሳሰባት ትገልጻለች።
    ለአንድ ሳምንት ያህል የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ የምግብ እርዳ የገባ ሲሆን፤ እስራኤል እና ሐማስ የሚያደርጉት ጦርነት ከቀጠለ የጋዛ ሕዝብ ለከፋ ረሃብ እንደሚጋለጥ የተባበሩት መንግሥታት እያሳሰበ ይገኛል።
    አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ድርድር እየተደረገ ሲሆን ረቡዕ የነበረው ስብሰባ ያለስኬት ተጠናቋል።
    ሐማስ ባወጣው መግለጫ “ሙሉ በሙሉ ጥቃቱ እስካልቆመ ድረስ ስለ እስረኞችም ሆነ ስለ ታጋቾች ልውውጥ ንግግረእ አይኖርም የሚለው የፍልስጤም ብሔራዊ ውሳኔ ነው” ብሏል።
    መግለጫው ሌላ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድንን ያማከለ ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም። ኢስላሚክ ጂሃድ የተሰኘው አነስ ያለ ቡድን ከሐማስ በተጨማሪ እስራኤላዊያንን አግተው ከያዙ መካከል ነው።
    የሐማስ መግለጫ የእስራኤል መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነው።
    እስራኤል እንደምትለው ከሐማስ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ብቸኛው አማራጭ ወታደራዊ እርምጃና የነብስ አድን ሥራ ነው።
    ነገር ግን ይህን እርምጃ እስካሁን ድረስ ብዙም ውጤታማ አይደለም።
    እሰራኤል እስካሁን ኦሪ ሜጊዲሽ የተባለ አንድ ታጋች ብቻ ነው እስካሁን ማስለቀቅ የቻለችው።
    የእስራኤል መንግሥት ታግተው ከተወሰዱ እስራኤላዊያን ቤተሰቦች ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ሲሆን አንዳንዶች ኃይል መጠቀም አማራጭ አይደለም ይላሉ።
    ነገር ግን እስራኤል ጦርነቱን ብታቆም ሐማስ ሙሉ በሙሉ ወታራዊ እንቅስቃሴዎቹን ያቆማል ወይ የሚለው ሌላኛው ጥያቄ ነው።
    የእስራኤል መንግሥት ደግሞ የሐማስን አቅም ክፉኛ ካላደቀቀ በቀር ጦርነቱን ለማቆም ዝግጁ አይደለም።
    ይህ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ላሉት የጋዛ ነዋሪዎች መልካም ዜና አይደለም።
    እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት 20 ሺህ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ ከሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከእነዚህም መካከል 8 ሺህ ሕፃናት እና 6200 ሴቶች ሲሆኑ ከ50 ሺህ በላይም ቆስለዋል።

0 Comments

Login to join the discussion