የታህሳስ 12 የምሽት ዜና

  • የብልጽግና ጦር በባሶ ሊበን ወረዳ በደረሰበት ሽንፈት ሲሸሽ ንጹሃንን መጨፍጨፉንና የአርሶ አደሩን ሰብል ማቃጠሉ ተሰምቷል ።
  • የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆችን ከስራ ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም ተጠይቋል፡፡ 
  • ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤት አባል በብልጽግና ካድሬዎች እየተሳደዱ መሆኑንም እንነግራችኋለን
  • የዕለቱ የጦር ግንባር ውሎ ምን ይመስላል የሚለውን መረጃ የባህርዳሩን የተኩስ ውሎ አጣቅሰን በዝርዝር እናስቃኛችኋለን፡፡

  • የባልደራስ መግለጫ
    የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆችን ከስራ ማፈናቀል በአስቸኳይ ይቁም ሲል ባልደራስ አሳሰበ
    "በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞችን በአዲስ መልክ እናደራጃለን በሚል ነባር ሠራተኞችን ያለ ፍላጎታቸው ፈተና እንዲፈተኑ አስገዳጅ ፎርም እንዲሞሉ ተደርገዋል" ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
    አስገዳጅ ፎርሙን የሞሉ ሰራተኞች በፈተናው ዙሪያም ሆነ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ ምክክርና ውይይት ባላደረጉበት ሁኔታ ፈተና ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው  ብቻ እንደተነገራቸውም አስፍሯል፡፡
    ከጽ/ቤት  እስከ ወረዳ መዋቅር ያሉ ሁሉም ሠራተኞች  ፈተናውን ማለፍ ያልቻሉ ሠራተኞች  "መቋቋሚያ" በሚል ክፍያ ከሥራ ገበታቸው እንደሚሰናበቱ  ባልደራስ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
    ‘’በከተማችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዳግባብነቱ ምላሽ ለመስጠት’’ በሚል የፖለቲካ ፈሊጥ የአዲስ አበባን ነዋሪና የአማራ ተወላጆችን ከሥራ የማፈናቀል ሤራ መሆኑን ከሠራተኞቹ አንደበት ለማወቅ ችያለሁም ሲል አክሏል።
    "የኦነግ/ኦሕዴድ ቡድን አማራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ይዟል፤ መቀነስ  አለበት በሚል ቅስቀሳ ያደርጉ እንደነበር የአደባባይ ሀቅ ነው" ያለው ፓርቲው  "ስለሆነም  የአዲስ አበባ ህዝብ ይህን እኩይ ከፋፋይ የጎሰኞች ሤራ ተቃውሞ ድምፁን በጋራ እንዲያሰማ" ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡
    ባልደራስ በዚህ መግለጫው "የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የሚደረገው ስልታዊ ማፈናቀል ባስቸኳይ እንዲቆም፣ የአማራን ሕዝብ በብቃት ማረጋገጫ ሽፋን ከመንግሥት ሥራ የማፈናቀል ድርጊት እንዲቆም፣ በአማራን ሕዝብ ላይ አገዛዙ እያካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ሁሉም ዜጋ እንዲቃወም፣ አገዛዙ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ እያካሄደ ያለውን ማዋከብ እንዲያቆም፣ አዲስ አበባን በአንድ ማህበረሰብ የበላይነት ለመግዛት የሚደረግ ሂደት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ አሁን የኦሕዴድ ብልፅግና የሸረበው "ፈተና" የሚለዉ ሤራ አማራዉን ከመንግሥት ሥራ የማስዎጣት ሤራ በመሆኑ  ከእነአካቴዉ እንዲሰረዝ እንጠይቃለን" ሲል ጠይቋል፡፡

  • የናትናኤል የችሎት ውሎ
    ወጣት ናትናኤል ያለምዘውድ ፍርድ ቤት ቀረበ
    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የወጣቶች ዘርፍ ሃላፊና የስራ አስፈታሚ አባል ወጣት ናትናኤል ያለምዘውድ ዛሬ ታህሳስ 12/2016 አራዳ  ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቧል፡፡
    ፖሊስ አቶ ናትናኤልን ሁከት እና ብጥብጥ በከተማው ላይ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ይዘናቸዋል በማለት የምርመራ መዝገቡን ስላላጠናቀቅኩ እንዲሁም ያልተያዙ ግብረ አበሮች ስላሉት ተጨማሪ 14 ቀናት ይሰጠኝ ሲል ፍ/ቤቱን ጠይቋል።
    በናትናኤል ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ  በኩል የቀረበው ክስ ከደንበኛቸው ጋር ምንም የማይገናኝ እና ሰላማዊ ሰው መሆናቸውን በመግለፅ  የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ተጠይቋል።
    ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ 10 የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ለታህሳስ 22/2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
    ናትኤል ያለምዘውድ ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 10/2016 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤቱ በአገዛዙ ሀይሎች ታፍኖ መወሰዱ ይታወቃል፡፡
    የግፍ እስረኛው ናትኤል ያለምዘውድ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ሶስተኛ  ፖሊስ ጣቢያ በግፍ እስር ላይ ይገኛል።

    • የፋኖ ድል ከምስራቅ ጎጃም

 የብልጽግና ጦር በባሶ ሊበን ወረዳ በደረሰበት ሽንፈት ሲሸሽ ንጹሃንን መጨፍጨፉንና የአርሶ አደሩን ሰብል ማቃጠሉን ነዋሪዎች ተናገሩ
በምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን ወረዳ የፋኖን ምት መቋቋም ያቃተው የብርሃኑ ጁላ ጦር አካባቢዎቹን ለቆ ሲሸሽ በንጹኀን ላይ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጭፍጨፋ መፈጸሙንና የአርሶ አደሩን ሰብል በእሳት በማቃጠል ማውደሙን የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠዋል፡፡
እማኞች በሰጡት ቃል ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ የወረዳውን ሰፊ አካባቢ ፋኖ መቆጣጠሩን ተከትሎ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን በመግለጽ በባሾ ሊበን ወረዳ የዱግ ቀበሌ የብልጽግና ጦር ከባድ መሳሪያ በማቀጣጠልና እሳት በመለኮስ የአርሶ አደሩን የስንዴ ሰብል ማውዳማቸውን አስረድተዋል፡፡
የብርሃኑ ጁላ ታጣቂዎች መሃል ከተማ በሚገኘ ቴክኒክና ሙያ ግቢው ውስጥ ዙሪያውን ምሽግ በመስራት እስከ ዛሬ ከሰዓት ድረስ ተኩስ መክፈታቸውን የነገሩን ነዋሪዎች ከቀናት በፊት ምድረ ገነት በተባለ ሆቴል ውስጥ አንድን በቀን ስራ የሚተዳደር ወጣት የብልጽግና ወታደሮች በጥይት መግደላቸውን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና በፋኖ ሲሸነፍ ንጹሃን ላይ የሚፈጽመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ አስደንጋጭ መሆኑንም እማኞች ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በሰጡት ቃል ይህን ያህል አማራን ለማጥፋት መነሳቱ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል፡፡


  • የህዝብ ተመራጩ ተቃውሞ

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የምክር ቤት አባል በብልጽግና ካድሬዎች እየተሳደዱ መሆኑን ተናገሩ

በቅርቡ የተመሠረተው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው ላይ የጉራጌን በክልል የመደራጀት ጥያቄን በማንሳት የሚታወቁት የአቶ ታረቀኝ ደግፌን ያለመከሰስ መብት አንስቷል። ይህንን ተከትሎም የህዝብ ተመራጩ አቶ ታረቀኝ ደግፌ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
አቶ ታረቀኝ በስልክ በሰጡት ማብራርያ የህዝብ ተመራጭን የተለየ ሃሳብ ምክር ቤቱ መስማት አልፈልግም ማለት የትም አያደርስም ብለዋል፡፡
አቶ ታረቀኝ ተቃውሟቸውን በገለፁበት ንግግራቸው ህዝብን ወክዬ የክልል ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ብሆንም የተለየ ሃሳብ በማንሳቴ ብቻ ለእስር ተዳርጌ ነበር ያሉ ሲሆን አሁንም እየተሳደድኩ ነው ብለዋል፡፡
የህዝብ ድምፅ በማስጋባታቸው ምክንያት ያለመከሰስ መብታቸው እንደተነሳ የሚናገሩት የህዝብ ተወካዩ በዚህም የተለያዩ ጫናዎች እየደረሱባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሰላም እና ደህንነት ይረጋገጥ ስላልኩ መሳደድ አልነበረብኝም ያሉት አቶ ታረቀኝ በምክር ቤቱ አማራጭ ሃሳብ የመጥላት እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የህዝብ ተመራጩ አክለውም ያለመከሰስ መብቴ የተነሳው የተለየ ሃሳብ በመፍራት እውነተኛ የህዝብ ተወካዮችን ከውክልና ለማራቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኔም ሆነ በቤተሰቦቼ ላይ ጫና እየሰረሰ ነው ሲሉ የተናገሩት አቶ ታረቀኝ ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በርካታ ወጣቶች ጫና እየደረሰባቸው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አክለውም በአከባቢያቸው የሚታየው ችግር በሌሎች ክፍሎች እየታየ መሆኑን አንስተው ለፍትህ ስርአቱ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

  • የቀጠለው ከባድ ውጊያ
    በአማራ ክልል የሸዋና የጎጃም አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው
    በዛሬው ዕለት ከቀኑ 4:00 ሰአት አካባቢ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በቀወት ወረዳ ራሳ ቀበሌ ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ውሏል፡፡
    በዚህ ትንቅንቅ በታየበት በፋኖ እና በብልጽግና ሰራዊት ውጊያም በታላላቅ ገድልና ጀብዱ የምትታወቀው የሸ አናብስቶች መገኛዋ ራሳ በፋኖ ስር ገብታለች፡፡
    የብልጽግና ወታደርም በደረሰበት ከባድ ሽንፈት ምክንያት የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቶ ሲፈረጥጥ ታይቷል፡፡ በየስፍራውም ተበትኗል፡፡ ፋኖም ይህን የአገዛዙን ሰራዊት እየተከተለ ሸዋ ሮቢት ድረስ ያመራ ሲሆን በከተማዋ ዙሪያም ከባድ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ የሮሃ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
    አሁን ላይም ጦርነቱ ወደ ሸዋሮቢት ከተማ የተዛመተ ሲሆን፣ በከተማዋ ዙሪያም ሀይለኛ ጦርነት እየተካሄደ ነው።
    በተጨማሪም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ማርዬና ድማምዬ በተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በእንቧይና በዋንዛ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡
    የከተማዋ የሮሃ ምንጮች እንደነገሩን ከሆነ በዛሬው እለት በከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት የታየ ሲሆን ፣ ማረሚያ ቤቱ ላይም ከባድ ጥበቃ እየተደረገ ነው፡፡
    ሸዋ ሮቢት ዙሪያዋም ከማለዳው በጀመረው ውጊያ እየተናጠች ነው፡፡
    በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የመሸገው የአገዛዙ ሃይል በፋኖ የደፈጣ ጥቃት ተፈጽሞበት ብትንትኑ መውጣቱ ታውቋል፡፡
    ፋኖም በካምፕ ውስጥ ካደረሰው ጥቃት በኋላ በርካታ ትጥቅ መማረክ ችሏል፡፡ እንዲሁም በከተማው የሚገኙ ሚሊሻና አድማ ብተና ፖሊሶችን ይዞ ሄዷል፡፡ በቡሬ ከባድ ውጊያ ይነሳል በሚል ስጋትም አገዛዙ በርካታ ሃይል እያስገባ ነው፡፡
    በዚሁ በምዕራብ ጎጃም የምትገኘው የደጋ ዳሞቷ ፈረስ ቤት ከተማም እስካሁን በፋኖ እጅ ናት፡፡ በከተማዋ ዙሪያ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑንም ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በከተማዋ ሶስት አቅጣጫዎች የብልጽግና ሃይል ለመግባት ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም፡፡
    በምስራቅ ጎጃም አማኑኤል ከተማም ለሶስት ቀናት የዘለቀ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ፋኖም በትናንትናው እለት ወደ ከተማዋ ገብቶ የሚፈልገውን ኦፕሬሽን ሰርቶ መውጣቱ ነው የታወቀው፡፡
    ነገር ግን የአገዛዙ ሃይል በንጹሃን ላይ ግድያ መፈጸሙ ታዉቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በማቻከሏ አማኑኤል ከተማ ከባድ ትንቅንቅ እንዳለ ነው፡፡

0 Comments

Login to join the discussion