የታህሳስ 13 የምሽት ዜና

  • ከወለጋ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡ 
  • የጉራጌ ተወላጆችና ፖለቲከኞች እስር አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
  • በአማራ ክልል ያለው ውጊያ በርትቷል፤ ከየከተሞቹ እየሸሹ ስላሉ የብልጽግና ባልስልጣናትም የምንላችሁ አለን፡፡ 
  • ትልቋን ከተማ የተቀማነው በግዴለሽ ኮማንደሮች ነው ሲሉ ስለወቀሱት ጀነራልም የምንላችሁ ነገር አለን፡፡

  • የአመራሮቹ እስር
    ጎጎት ፓርቲ በአመራሮቼ ላይ የሚፈጸመው ህገወጥ እስር ቀጥሏል ሲል አስታወቀ
    ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ  "በፓርቲያችን አመራሮች ላይ የሚደረገው ህገ ወጥ እስር እንደቀጠለ ነው" ሲል ገለጿል፡፡
    ፓርቲው "የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ መስፍን አበራ ታህሳስ 8 ሌሊት ወልቂጤ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ታፍነው ሲወሰዱ ዛሬ ታህሳስ 13 ደግሞ አቶ ጌዲዮን ቦጋለ ከአዲስ አበባ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደዋል"  ሲል በማህበራዊ ትስስር ገፆቹ አስታውቋል።
    በተመሠሣይ ዛሬ ሌሊት 12:00  የፓርቲው የማዕከላዊ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መላኩ ይርዳው በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው መወሰዳቸው ተሰምቷል፡፡
    ፓርቲው "በአመራሮቻችን ላይ የሚፈፀመው እስር ፓርቲውን ለማዳከም ያለመ ነው። ሁሉም አመራሮች በሚታሰሩበት ወቅት በፓርቲው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ የክስ ጭብጥ ሆኖ ሲቀርብ በተደጋጋሚ እያየን ነው።" ሲል አክሎ ገልፆል።
    ጎጎት መንግስት ነኝ ባዩ አካል ያስቀመጠው ህጋዊ የትግል ሜዳ መሰረት በማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስቶ አገዛዙ እና ተባባሪዎቹ ግን ፓርቲውን በእንጭጩ መቅጨት የሚል የተቀናጀ ዘመቻ ከፍተው በግልፅ እና በስውር እየሰሩ ይገኛሉ ስል አስታውቋል።
    ፓርቲው አክሎም "የህዝባችን መብት እስኪከበር ሰላማዊ እና ህጋዊ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብሏል።

  • የወለጋ ተፈናቃዮች መከራና ስጋት
    የወለጋ ተፈናቃዮች "እዚህ ረሃብ ነው ፣ እዛ ብንሄድ ግን ሞት ነው የሚጠብቀን" ሲሉ ወደ ወለጋ እንደማይመለሱ ገለጹ
    ከተለያዩ የወለጋ ዞኖቾች ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ እንዲሁም በደቡብ ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ያለፈቃዳችን ጥቃት ሸሽተን ወደመጣንበት አካባቢ እንድንመለስ ተገደናል ሲሉ ነግረውኛል ይላል ቢቢሲ በዘገባው።
    የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት አመራሮች በበኩላቸው ተፈናቃዮች በግዳጅ እንዲመለሱ እንደማይደረግና የሚመለሱት ሰዎች ሰላማዊ ወደሆኑ የወለጋ አካባቢዎች ይላሉ፡፡
    የክልሉ አመራሮች ይህን ይበሉ እንጂ በገራዶ፣ ደጋን፣ ጃሪ፣ ኩታበር፣ ሐይቅና ሌሎችም መጠለያዎች ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተፈናቃዮች ለደኅንነታቸው ዋስትና ወደማያገኙበት አካባቢዎች እንዲመለሱ እየተገደዱ መሆኑን ነው።
    ቢቢሲ ያነጋገራቸው በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃዮች “ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ለመመለስ ፍላጎት ባይኖረንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቀያችን እንደምንመለስ ተነግሮናል” ይላሉ።
    “የመጣችሁበት ቦታ አሁን ሰላም አለ፤ ትሄዳላችሁ ተባልን። ጉዟችን የፊታችን ሰኞ ታኅሣስ 15 2016 ዓ.ም.ከሰዓት እንደሆነ ተነግሮናል። መመለስ እንፈልጋለን ግን ሰላም የለም። ሰላም አለ የሚሉት የውሸት ነው። እኛ እኮ እዛ ከቀሩ ወገኖቻችን መረጃ ቀን በቀን እናገኛለን። እራሳቸውን እየጠበቁ እና እየተከላከሉ ነው የሚኖሩት” ብለዋል አንድ ተፈናቃይ።
    “በዛ ያሉ ሰዎች ገበያ ከወጡ፣ ሕክምና ካገኙ ሦስት ዓመት አልፏቸዋል። ከወረዳው አስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም” በማለት የአካባቢውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
    ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከነገ በስቲያ ሰኞ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የማይመለሱ ከሆነ አሁን ከሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በግዳጅ እንዲወጡ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
    “እዚህ ረሃብ ነው። እዛ ብንሄድ ደግሞ ሞት ነው” የሚጠብቀን የሚሉት ተፈናቃይ ደግሞ አሁን ተጠልለው ባሉት ጣቢያ የዕርዳታ ምግብ ለመጨረሻ ግዜ የተሰጣቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መሆኑን ይናገራሉ።
    “እዛ ያሉ  ሰዎች ጋር ስንደውል በስጋት ነው የሚኖሩት። ወፍጮ እንኳ የለም፤ በድንጋይ እየፈጩ ነው ሕይወታቸውን እያቆዩ ያሉት። ጨው እና በርበሬ ካገኙ ስንት ዓመት አለፋቸው” ይላሉ።
    ወደቀያቸው መመለስ ቢፈልጉም ያ እንዲሆን የሚሹት ግን ሰላም ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
    “ስንት ወላጆቻችን፤ ሕጻናቶቻችን እና ሴቶች አልቀውብን አሁንም እንዴት ሰላም ወደሌለበት ቦታ እንሄዳለን?” ብለን ስንጠይቅ ከታኅሳስ 15 እስከ 17 መጠለያውን ካለቀቃችሁ የሚመለከተው አካል መጥቶ ያስወጣችኋል” ብለውናል በማለት ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት ይገልጻሉ።
    ሮሃ በትናንትናው እለት ያነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች ደግሞ ወደ ወለጋ አካባቢዎች መመለሳቸውን በሚመለከት ይህን ብለው ነበር፡፡
    የምስራቅ አማራ ፋኖ አዛዥ ምሬ ወዳጆና የአማራ ህዝባዊ ሃይል የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ጠበቃ አስረስ ማረ እነዚህ የአማራ ተወላጆች ወደ ሞት ቀጠና እንዲሄዱ እንደማይፈቅዱ ለሮሃ ተናግረዋል፡፡


  • የአልቡርሃን ዛቻና የሱዳን ኮማንደሮች
    አል-ቡርሐን ዋድ ማዳኒ ከተማን በቸልተኝነት አስይዘዋል ባሏቸዋ ኮማንደሮች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናገሩ
    የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን ዋድ ማዳኒ ከተማ በፈጥኖ ደራሽ  ኃይሎች እጅ የወደቀችው “በችላ ባይ” ኮማንደሮች ምክንያት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
    የገዚራ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ዋድ ማዳኒን ጦሩ ጥሎ የወጣው ለመከላከል በቂ ጥረት ሳያደርግ ነው ብለዋል።
    ገዚራ ላለፉት ስምንት ወራት ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ተደርጎ ስለተወሰደ ከ300,000 በላይ ሰዎች ተጠልለውበታል።
    ዋድ ማዳኒ ከተማ ከተያዘች በኋላ አል-ቡርሐን በይፋ ንግግር ሲያደርጉ የመጀመሪያው ነው።
    “እያንዳንዱን ችላ ባይ ኮማንደር ተጠያቂ እናደርጋለን። ከተማዋን ለቀው የወጡ ያለ ርህራሄ ተጠያቂ መደረጋቸው አይቀርም” ብለዋል።
    ጦሩ እንዴት “ድንገት ከከተማዋ እንደወጣ” ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል።
    ጦሩ በመውጣቱ ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ከተማዋን መቆጣጠር ችሏል።
    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አጠቃላይ ገዚራ ግዛትን እንደተቆጣጠረ እየገለጸ ይገኛል፡፡
    ግጭት ሊባባስ ይችላል በሚል ፍራቻ በአቅራቢያው ያሉ የተራድኦ ሠራተኞች ለቀው እየወጡ ነው።
    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሱዳን መዲና ካርቱምን እና የዳርፉር ግዛትን 70 በመቶ መያዙ ይነገራል።
    ከተማዋ እርዳታ የሚሰጥባት በመሆንም ካርቱምን ተክታ ነበር።
    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን ሲቆጣጠር ግን እርዳታ ሰጭዎች ሸሽተው ወጥተዋል።
    ከከተማዋ የሸሹ ሲቪሎችና እርዳታ ሰጭዎች አሁን በገዳሪፍ፣ ሰነርና ዋይት ናይል ግዛቶች ለመጠለል ተገደዋል።
    “ሁሉም ሰው ተደናግጧል። በገዳሪፍ ያሉትም ሳይቀሩ ጦርነቱ እዛ እንደሚደርስ ሰግተዋል” ይላል።
    የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ወደ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ገደማ በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለዋል።
    የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ እንደሚሉት የሱዳን ጦርነት በዓለም ከፍተኛው የተፈናቃዮች ቁጥር የሚመዘገብበት ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

  • የፋኖ እና የአገዛዙ ጦር ፍጥጫ
    ፋኖ የተዳከመውን የብልጽግናን ሰራዊት በሰሞኑ ውጊያዎች ማፈራረሱ ተሰማ
    በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሰሞኑ የተደረገውን ከባድ ውጊያ ተከትሎ የብልጽግና ሰራዊት በከፍተኛ ሁኔታ ሲዳከም ፋኖ ደግሞ ያሰባቸውን አላማዎች አሳክቶበታል፡፡በአንጻሩ ደግሞ የአገዛዙ ጦር ንጹሃንን በድሮን እና በከባድ መሳሪያ እየጨፈጨፈ ነው፡፡
    በዚህም በምስራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ በፋኖ እጅ መግባቷን ተከትሎ ብልጽግና በከተማዋ ላይ የድሮን ጭፍጨፋ እየፈጸመ ነው፡፡
    ፋኖ የጁቤን ተቆጣጥሮ የአገዛዙን ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ ማድረጉን ተከትሎ እነ ብርሃኑ ጁላ በቃላቸው መሰረት ህዝቡን በከባድ መሳሪያና በድሮን እየፈጁት ነው፡፡
    የብልጽግና ሰራዊት ያለ ርህራሄ የከተማዋን ህዝብ በከባድ መሳሪያና በድሮን መጨፍጨፉን ተከትሎም ፋኖ ወደ ከተማዋ የገባበትን ኦፕሬሽን አጠናቆ ወጥቷል፡፡
    በትናንትናው ምሽትም የድሮን ጥይቶቹን በክሊኒክና በሱቆች ላይ መጣሉ ነው የተሰማው፡፡ በዚህም በርካታ ንጹሃን ሞተዋል፡፡
    በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ገብቶ የነበረው የጎጃም እዝ ፋኖ ከተማዋን ለቆ ወጥቷል፡፡ ከተማዋን ያለውጊያና ያለተኩስ ልውውጥ ለቀው መውጣታቸውን የነገሩን የፋኖ አባላት ፣ወደ ከተማዋ የገባቡበትን አላማ አሳክተው መውጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
    አሁን ላይም በከተማዋ ያለው ውጊያ መብረዱ የታወቀ ሲሆን ፣ የብልጽግና ሰራዊትም በስጋት ምክንያት ወደ ከተማዋ ዘልቆ መግባት ፈርቷል ብለውናል፡፡
    ከሰኞ እስከ አርብ የተካሄደው የፈርስ ቤትና የአካባቢዋ ውጊያም ጋብ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
    በሌላ በኩል በትናንትናው እለት ፋኖ በሰሜን ሸዋ ከራሳ ፣ ከማርዬ ፣ ከሰንበቴ አቅጣጫዎች በመነሳት ወደ ሸዋሮቢት ከተማ መግባቱ ይታወቃል፡፡ በሸዋ ሮቢት ዙሪያ በትናንትናው እለት እልህ አስጨራሽ ውጊያ ከተደረገ በኋላ አናብስቶቹ የሸዋ ፋኖዎች ወደ ቀወት ወረዳ ዋና ከተማዋ ሸዋ ሮቢት ሰተት ብለው ገብተዋል፡፡ ከገቡ በኋላም ለሰዓታት የቆየ ኦፕሬሽን አካሂደው ከተማዋ ላይ እልቂት እንዳይመጣ በሚል ለቀው ወጥተዋል፡፡
    ነገር ግን ዛሬ ማለዳ ድረስም በከተማዋ ድልድይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ፋኖዎች እንደነበሩና የብልጽግና ሰራዊት ወደ ከተማዋ እንዳይደርስ እንዳደረጉት ምንጮ ገልጸዋል፡፡
    እንዲሁም ዙጢ ፣ ጀጀባና ማርዬ በሚባሉ አካባቢዎች ዛሬም በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ሲደረግ የዋለ መሆኑ ታውቋል፡፡
    የቀወት ወረዳና የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ባልስልጣናትም እግሬ አውጪኝ ብለው ወደ ከሚሴ ፈርጥጠዋል፡፡ በመከላከያና በአድማ ብተና ተከበው የሸሹት ባልስልጣናቱም ለጥቂት ከፋኖ በትር ማምለጣቸውን ነው የሰማነው፡፡
    በከተማዋ አሁንም ከባድ ውጥረት ያለ ሲሆን የብልጽግና ታጣቂዎችም በከተማዋ እንደማይገኙ ተሰምቷል፡፡
    ይሁን እንጂ የአገዛዙ ሰራዊት በዚህ ውጊያ ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ከተማዋ ተኩሶ በርካታ ንጹሃንን ገድሏል፡፡
    የፋኖ አባላት በያዝነው ሳምንት በምስራቅ ጎጃም ማቻከል ወረዳ አማኑኤል ከተማ ፣ በዚሁ ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ የጁቤ ከተማ ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ ፣ በሰሜን ሸዋ ቀወት ወረዳ ሸዋ ሮቢት ከተማ ፣ በደቡብ ጎንደር ሃሙሲት ከተማ ገብተው ወጥተዋል፡፡
    በባህርዳርና በመሳሰሉ አካባቢዎች ደግሞ ኦፕሬሽኖችን ሰርተዋል፡፡
    ታዲያ ይህን በሚመለከት ሮሃ ያነጋገረቻቸው የፋኖ አባላት ወደ ከተሞቹ ገብተው የወጡበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡
    በዚህም ብልጽግና ሆድ አደሮችን ተጠቅሞ በየአካብቢዎቹ መዋቅር ለመዘርጋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ  ማስቆም አንደኛው አላማ ሲሆን ፣ ሌላኛው ደግሞ የደከመውን የብልጽናን ጦር ሞት ለማፋጠን ነው ብለዋል፡፡
    ከዚህም በተጨማሪ ማን ነው እጅ ሰጪ የሚለውን ለማሳየት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡በመሆኑም አላማቸው እንደተሳካ አሳውቀዋል፡፡
    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፋኖ በባህርዳር ቀበሌ 14 ትናንት በሰራው ኦፕሬሽን የተገደሉ በርካታ የሚሊሻ አባላት በዛሬው እለት መቀበራቸው ተሰምቷል፡፡
    በዚህም ብልጽግና የአካብቢው ሰው ወጥቶ በግድ እንዲቀብር አዞ ነበር ተብሏል፡፡ ነገር ግን የወጣ ህዝብ እንደሌል ነው የተሰማው፡፡
    በከተማዋ ትናንት ከሰዓቱን ፋኖ ሰንጥቆ ገብቶ በቦምብና በተኩስ የብልጽግና ሰራዊትን መግቢያ መውጪያ አሳጥቶ ውሏል፡፡ ከዚህም ባለፈ ምሽት ድረስ ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በርካታ ባልስልጣኖችም ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው፡፡

0 Comments

Login to join the discussion