የወለጋ ተፈናቃዮች ሰቆቃ

  • የወለጋ ተፈናቃዮች "እዚህ ረሃብ ነው ፣ እዛ ብንሄድ ግን ሞት ነው የሚጠብቀን" ሲሉ ወደ ወለጋ እንደማይመለሱ ገለፁ።

    ከተለያዩ የወለጋ ዞኖቾች ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ እንዲሁም በደቡብ ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ያለፈቃዳችን ጥቃት ሸሽተን ወደመጣንበት አካባቢ እንድንመለስ ተገደናል ሲሉ ነግረውኛል ይላል ቢቢሲ በዘገባው።
    የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት አመራሮች በበኩላቸው ተፈናቃዮች በግዳጅ እንዲመለሱ እንደማይደረግና የሚመለሱት ሰዎች ሰላማዊ ወደሆኑ የወለጋ አካባቢዎች ይላሉ፡፡
    የክልሉ አመራሮች ይህን ይበሉ እንጂ በገራዶ፣ ደጋን፣ ጃሪ፣ ኩታበር፣ ሐይቅና ሌሎችም መጠለያዎች ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተፈናቃዮች ለደኅንነታቸው ዋስትና ወደማያገኙበት አካባቢዎች እንዲመለሱ እየተገደዱ መሆኑን ነው።
    ሮሃ ያነጋገረቻቸው በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃዮች “ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ለመመለስ ፍላጎት ባይኖረንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቀያችን እንደምንመለስ ተነግሮናል” ይላሉ።
    “የመጣችሁበት ቦታ አሁን ሰላም አለ፤ ትሄዳላችሁ ተባልን። ጉዟችን የፊታችን ሰኞ ታኅሣስ 15 2016 ዓ.ም.ከሰዓት እንደሆነ ተነግሮናል። መመለስ እንፈልጋለን ግን ሰላም የለም። ሰላም አለ የሚሉት የውሸት ነው። እኛ እኮ እዛ ከቀሩ ወገኖቻችን መረጃ ቀን በቀን እናገኛለን። እራሳቸውን እየጠበቁ እና እየተከላከሉ ነው የሚኖሩት” ብለዋል አንድ ተፈናቃይ።
    “በዛ ያሉ ሰዎች ገበያ ከወጡ፣ ሕክምና ካገኙ ሦስት ዓመት አልፏቸዋል። ከወረዳው አስተዳደር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም” በማለት የአካባቢውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
    ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከነገ በስቲያ ሰኞ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የማይመለሱ ከሆነ አሁን ከሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ በግዳጅ እንዲወጡ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
    “እዚህ ረሃብ ነው። እዛ ብንሄድ ደግሞ ሞት ነው” የሚጠብቀን የሚሉት ተፈናቃይ ደግሞ አሁን ተጠልለው ባሉት ጣቢያ የዕርዳታ ምግብ ለመጨረሻ ግዜ የተሰጣቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መሆኑን ይናገራሉ።
    “እዛ ያሉ  ሰዎች ጋር ስንደውል በስጋት ነው የሚኖሩት። ወፍጮ እንኳ የለም፤ በድንጋይ እየፈጩ ነው ሕይወታቸውን እያቆዩ ያሉት። ጨው እና በርበሬ ካገኙ ስንት ዓመት አለፋቸው” ይላሉ።
    ወደቀያቸው መመለስ ቢፈልጉም ያ እንዲሆን የሚሹት ግን ሰላም ሲሰፍን ብቻ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
    “ስንት ወላጆቻችን፤ ሕጻናቶቻችን እና ሴቶች አልቀውብን አሁንም እንዴት ሰላም ወደሌለበት ቦታ እንሄዳለን?” ብለን ስንጠይቅ ከታኅሳስ 15 እስከ 17 መጠለያውን ካለቀቃችሁ የሚመለከተው አካል መጥቶ ያስወጣችኋል” ብለውናል በማለት ሌላ ተፈናቃይ ደግሞ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት ይገልጻሉ።
    የምስራቅ አማራ ፋኖ አዛዥ ምሬ ወዳጆና የአማራ ህዝባዊ ሃይል የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ጠበቃ አስረስ ማረ እነዚህ የአማራ ተወላጆች ወደ ሞት ቀጠና እንዲሄዱ እንደማይፈቅዱ ለሮሃ ተናግረዋል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion