የተጋለጠው የመርዓዊ ጭፍጨፋ

በመርዓዊ ከተማ  በተፈጸመ የግፍ ጭፍጨፋ ከ100 የሚበልጡ ንጹሃን ሰዎች በአገዛዙ ሃይሎች መገደላቸውን ቢቢሲ አጋለጠ
ከክልሉ ዋና ከተማ ከባሕር ዳር በ35 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው መርዓዊ ከተማ በአገዛዙ ሃይሎች እና በፋኖ መካከል የተደረገ ውጊያን ተከትሎ በነዋሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት፣ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ነዋሪዎችን ፣ የሟች ሜተሰቦችንና እማኞችን አነጋግሮ ዘገባ ሰርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባሕር ዳር ቢሮ በመርዓዊ ከተማ በንጹሃን ላይ ጥቃት እንደደረሰ ከተለያዩ ምንጮች መረጃው እንደደረሰው፣ ክትትል እና ምርመራም እያከናወነ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ ባለፉት ቀናት የሆስፒታል ምንጭን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ቢቢሲ ያነጋገረ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ግድያው የተፈጸመው በቤታቸው እና በመንገድ ላይ በተገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰኞ ጥር 20/2016 ዓ.ም. ከጥቃቱ ቀደም ብሎ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በአገዛዙ ጦር እና በፋኖ  መካከል “ከባድ ውጊያ” እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ያንን ተከትሎ ከ50 እስከ 100 የሚደርሱ ንጹሃን  ሰዎች በብልጽግና ጦር “ተረሽነዋል” ብለዋል።ይህ ጥቃት የተፈጸመው ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ ፋኖዎች ከተማዋን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ “መከላከያ ሠራዊት ቤት ለቤት በመዞር እና መንገድ ላይ ያገኛቸውን ሰዎች መረሸኑን” የተናገሩት የዐይን እማኞች፤ ጥቃቱ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት የዘለቀ ነበር ብለዋል።በቀን ሥራ ይተዳደር የነበረ የአራት ልጆች አባት የሆነ ወንድማቸው እንደተገደለባቸው የሚናገሩ ነዋሪ “መጀመሪያ እኔ ቤት መጥተው ሲፈትሹ ‘የቤተ-ክርስትያን ሰው ነኝ’ ስላቸው ወጥተው ሄዱ። ቀጥለው ወንድሜ ቤት ገብተው ይዘውት ሄዱ” ይላሉ፡፡ወንድማቸው ለጥያቄ ተወስዶ ይመለሳል ብለው እየጠበቁ የነበሩት ነዋሪ፣ ከሌሎች ጋር በሰደፍ እና በቆመጥ እየተደበደቡ ሲወሰዱ እና ሲገድሏቸው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
“አንዱን ልጅ በአምስት ጥይት እዚያው ሰፈራችን ኮብሉ ላይ ገድለው ጣሉት። ወንድሜን እና ሌሎች ሰዎችን ደግሞ ሰብስበው አንድ ላይ 13 ሰዎች ወደ አስፓልት ይዘው ወጥተው ገደሏቸው። …ፊታችን ስለገደሏቸው ነው ያመንነው” ብለዋል።
ይህንኑ ክስተት በተመለከተ አንድ የህክምና ባለሙያ 13ቱ ሰዎች ከአስፓልት ዳር መገደላቸውን እንደሚያውቁ ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ በአጠቃላይ በከተማዋ ውስጥ በዚያ ዕለት 85 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ሌላ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ እና ታናሽ ወንድማቸው እንደተገደለባቸው የሚናገሩት የመንግሥት ሠራተኛ ወንድማቸው ከልጁ እቅፍ ተነጥሎ ተወስዶ “በጭካኔ ተረሽኖብኛል” ብለዋል።“ወንድሜን ልጁን ይዞ ከተቀመጠበት ቤቱ ተወስዶ ነው የተገደለው። ባለቤቱ ‘ህጻኑን ተቀበይ ተብዬ ተገደድኩ፤ ህጻኑን ተቀበልኩት።…ዐይኔ እያየ ነው ግንባሩ ብለው መንገድ ላይ የገደሉት። አብሮት የነበረውንም ጓደኛውን ገድለውታል’ ብላ ነግራኛለች።” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ከወንድማቸው ባሻገርም በዕለቱ መንገድ ላይ 50 የሚሆኑ ሰዎችን አስከሬን መመልከታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም “በየመንገዱ እና በየጥሻው” በርካታ ሰው ሳይገደሉ እንዳልቀረ ገምተዋል።
ሌላ የዐይን እማኝ ደግሞ በበርካታ ቀብሮች ላይ መገኘታቸውን ጠቅሰው የሟቾችን ቁጥር ከ100 በላይ አድርገዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ጥር 21/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ 48 አስከሬን መቆጠራቸውን የሚናገሩ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪ፤ “ከማርዘነብ ሆቴል እስከ በረድ ወንዝ ድረስ ግራ እና ቀኝ አስከሬን ብቻ ነበር” ብለዋል።
የሟቾችን ቁጥር 115 ገደማ የሚያደርሱ አንድ የዐይን እማኝ መከላከያ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ስታዲየም እና ጤና ጣቢያ በተባሉ ሰፈሮች “ከስድስት ዓመት ህጻን እስከ 75 ዓመት አዛውንት” ድረስ ግድያ ተፈጽሟል ይላሉ።
የሆስፒታል ሠራተኛ የሆኑት የዐይን እማኝ በከተማዋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የስድስት ወር ነፍሰ ጡርን ጨምሮ 25 ሰዎች ቆስለው መጥተው “የተረፈ የለም” ይላሉ።
“24ቱ ሆስፒታል የመጡት ሞተው ነው። አንዲት የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ሴት ከነ ነፍሷ መጥታ ሆስፒታል እንደደረሰች አርፋለች። አጠቃላይ 25 ነበር የመጡት” ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት ከቤት ለቤት አሰሳው ባሻገር የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ መንገድ ላይ የተገኙ ሰዎችን እና የቀን ሠራተኞችን “በበቀል አንበርክኮ” ረሸኗል ሲሉ ነዋሪዎች፣ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ በሁለት ስፍራ ላይ ሰፍሮ ከሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በከተማዋ አስተዳደር ህንጻ ውስጥ በነበሩት ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ሰኞ ጠዋት ለፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ምላሽ የተወሰደ “የበቀል እርምጃ” ለበርካታ ሰዎች ግድያ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ፋኖን አሳድራችኋል፤ ያስጠቃችሁን እናንተ ናችሁ፤ ፋኖን ትቀልባላችሁ” እያሉ “እየዛቱ” ነበር ያሉ አንድ ቤታቸው የተፈተሸ ነዋሪ፤ “ከመሞት መሰንበት” ብለን ዝም አልን ሲሉ ጥቃቱ የበቀል ነበር ብለዋል።
በርካታ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተገድለው ተጥለው በመቆየታቸው ዘግናኝ ሁኔታ መመልከታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው “የተገደሉ ሰዎች አስከሬንን ለመለየት እንኳ አስቸጋሪ ነበር” ይላሉ።
“አብዛኛው ሰው በአለባበሱ፣ በሰውነት ቅርጹ ነበር የሚለየው። አስከሬኖች በጥይት ክፉኛ ከመበሳሳታቸው በተጨማሪ፣ ማንሳት አይቻልም ተብሎ አንድ ቀን አሳድረዋቸዋል” ያሉ አንድ እማኝ መለየት አስቸጋሪ በመሆኑ በጅምላ ቀብር እንደተፈጸመ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እንደ ባህሉ እና ሥርዓቱ ለተገደሉት ሰዎች ተገቢው ቀብር አልተፈጸመም” ያሉት ነዋሪዎች፤ ሐዘን መቀመጥ እና ለቅሶ መድረስ አይታሰብም በማለት “የተፈጸመው ከግፍም በላይ ግፍ” ሲሉ ጥቃቱን ገልጸውታል።
በአካባቢው ሁለት አብያተ ክርስቲያናት “ሆን ተብሎ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ጉዳት ደርሶባቸዋል” የተባለ ሲሆን፣ የግል ንብረቶች እና 15 የሚሆኑ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ሆን ተብለው እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህ በርካታ ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት በከተማዋ በደማቅ ሁኔታ በየዓመቱ ጥር 21 የሚከበረው የማርያም ንግስ በዓል ዋዜማ በመከሰቱ ምክንያት ከተማዋ በሐዘን ተውጣ በዓሉ እንዳልተከበረም ነዋሪዎቹ አክለው ተናግረዋል።
በዚህ በመርዓዊው ጭፍጨፋ በርካታ ንጹሃን በግፍ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion