የሸዋው የድሮን ጭፍጨፋ

በሸዋ ሰላ ድንጋይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በርካታ ንጹሃን ተገደሉ
አገዛዙ በአማራ ህዝብ ላይ ይፋዊ ጦርነት ካወጀበት ከባለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ እስከዛሬዋ እለት ድረስ አለም ካፈራቻቸው የጦር መሳሪያዎች ውስጥ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም ሊባል በሚችል ደረጃ በህዝቡ ላይ አዝንቧል፡፡
ከክላሽ እስክ ስናይፐር ፣ ከሞርታር እስከ ድሽቃ ፣ ከብሬን እስከ ጀነራል መድፍ ተጠቅሞ የአማራ ወጣቶችን ፣ እናቶችን ፣ ህጻናት፣ አረጋውያንን ፣ ነብሰጡሮችን በጭካኔ ጨፍጭፏል፡፡
ድሮን እና የጦር ሄሊኮፕተር ተጠቅሞም ህጻናትን ሳይቀር ገድሏል፤ ቤተ እመነቶችን አውድሟል፡፡
ሆን ብሎ በሚያደርገውና ሁሌም እንደሚያደርገው በይፋ በገለጸው የድሮን ጭፍጨፋም በየከተሞቹ በርካታ ንጹሃን ተገድለዋል፡፡
ከ120 በላይ በሚሆኑት የድሮን ጥቃቶችም የሞቱ ንጹሃን ቁጥር እልፍ ነው፡፡ በዚህ ያልረኩት እነ ብርሃኑ ጁላም " አማራን በድሮን መግደላችንን እንቀጥልበታለን" ሲሉ በብሄራዊ ቴሌቪዥኑ በኩል በሰጡት ቃለ መጠይቅ በኩራት ተናግረው ነበር፡፡
ይህንንም ተከትሎ በትናንትናው ዕለት  የካቲት 11 ፡ 2016 ዓ.ም በሸዋ ሰላ ድንጋይ አካብቢ በህዝብ ትራንስፖርት  ሲጓዙ በነበሩ አንድ መኪና ሙሉ ንጹሃን አማሮች ላይ አገዛዙ እጅግ ዘግናኝ የድሮን ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡
በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ሰላ ድንጋይ አካባቢ ፣ሳሲት ልዩ ስሙ አንዲት ግራር፡ ፈላ መገንጠያ ላይ ክርስትና አስነስተው ወደ መኖሪያ ቀያቸው በአይሱዙ መኪና ሲመለሱ በነበሩ ከ60 በላይ ንጹን ናቸው በዚህ ጭፍጨፋ መፈጸሙን የሮሃ ምንጮች አረጋግጠውልናል፡፡
ጭፍጨፋውን አስመልክቶ ምላሽ የሰጠው የአካባቢው የፋኖ አመራር ፋኖ ኢሳያስ እንደተናገረው ደግሞ ፣ አገዛዙ ከሰሞኑ በነበረው ውጊያ በፋኖ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋውን መፈጸሙን ተናግሯል፡፡
በተመሳሳይ በአድማ ብተና እና በሚሊሻ እገዛ ንጹሃንን ከየቤቱ እያወጣ እየጨፈጨፈ መሆኑን ፋኖ ኢሳያስ ተናግሯል፡፡ በድሮን ጥቃቱም ከ50 በላይ ሰው መገደሉን አስታውቋል፡፡ እንዲሁም በሸዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን እና በዚህም አገዛዙ ያስገባው ሃይል እየተደመሰሰ ስለመሆኑ ገልጿል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion