የወሎ ቤተ አማራው ተጋድሎ

በአማራ ፋኖ የዕዝ ሰንሰለት በመናበብ ውጊያዎችን እያካሄደ መሆኑን የምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ አስታወቀ

በወሎ አማራው ግዛት በስፋት ከሚንቀሳቀሰው የአማራ ወታደራዊ ሃይል መካከል አንዱና ዋነኛው የሆነው የምስራቅ አማራ ፋኖ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ሰራዊት ባለቤት እንደሆነ ይታወቃል።

ይህ ሃይል በዋርካው ምሬ ወዳጆና በዕዙ ከፍተኛ ሃላፊዎች እየተመራ ከሰሜን እስከ ደቡብ የወሎ ግዛት ከፍተኛ ጀብዱ እየፈፀመ እንደሚገኝም ይገለፃል።

የምስራቅ አማራ ፋኖ የአንድነት ጉዞውን እንዲሁም በትግሉ የድጋፍና የእንቅፋት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ከጦርነቱ አውድ ጋር በማያያዝ በአመራሩ በኩል ማብራሪያ  ሰጥቷል።

የምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ ምክትል አዛዥ ፋኖ ረዳ ወይም አባአዝመራው በተለይም ለኢትዮ 251 በሰጠው ቃለመጠይቅ የዕዙን አደረጃጀትን በመስራት ጉዳይ  እንኳን እንደምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ እንደአማራ ፋኖ በአጠቃላይ በመናበብና በመረጃ ልውውጥ እንደሚንቀሳቀሱ አስረድቷል።

አገዛዙ ክፍፍል ለመፍጠርና ልዩነት ለማበጀት ቢሰራም እሱን በመመከትና አንድነትን አስጠብቆ በመዋጋት ከፍተኛ ድል መታየቱንም ፋኖ ረዳ አክሏል።

የአማራ ፋኖ የአንድነት ምክር ቤቱ ስራ መጀመሩንና ሁሉም የአማራ ፋኖ በወሎ አመራሮች አንድ ላይ መግለጫ የሚሰጡበት ቀን ቅርብ እንደሆነም ምክትል አዛዡ አረጋግጠዋል።ትግሉ አጋርና ደጋፊው ህዝቡ በመሆኑ በሀገር ውስጥ በውጭም ከቁራሽ እንጀራ ጀምሮ በዚሁ እንዲቀጥሉበትም ጥሪ ቀርቧል።

መከላከያው ጥሎ እየወጣ ባለበት ወቅት እንኳን ለፍርፋሪ ደመወዝ ብለው አገዛዙን እናድናለን ያሉ የአድማ ብተናና ሚሊሻ አባላት የትግሉ እንቅፋት በመሆናቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ምክትል አዛዡ ገልጿል።እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው በምስራቅ አማራ ፋኖ የመረጃ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኑ ሰራዊቱ እርምጃ እንደሚወስድም አፅንኦት ሰጥተዋል።



0 Comments

Login to join the discussion