የፌስቡክ አገልግሎት መቋረጥ

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ሜሴንጀር በመላው ዓለም መቋረጣቸው ድንጋጤ ፈጠረ

በሜታ ኩባንያ ስር የሚንቀሳቀሱት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ሜሴንጀር በመላው ዓለም በድንገት መቋረጣቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸው ድንጋጤን ፈጥሯል።

እነዚህ የማህበራዊ ትስስር አይነቶች መቋረጣቸው በተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰበር ዜና ሆኖ እየወጣ ቢሆንም ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ ለምን እንደተቋጡ ምክንያቱ አልታወቀም።

በኢትዮጵያም ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ሜሴንጀር አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸውን ሮሃ አረጋግጣለች።

ከአገልግሎቱ መቋረጥ በኋላ በተለይም በቲውተር ወይም በአዲሱ ስሙ X ገጾች እየተላለፉ የሚገኙ መረጃዎች በተጠቃሚዎች ዘንድ ሰፊ ሥጋት እንዲፈጠር አድርገዋል።
ነገር ግን የስህተት መልእክቶቹ በፌስቡክ የመግቢያ ሥርዓት ላይ ያሉ ችግሮች እንጂ የሃክ ወይም የሳይበር ጥቃት አለመሆናቸውን ዘኢንዲፔንደንት በዘገባው አስታውቋል።

በሜታ ባለቤትነት የተያዘው ዋትስአፕ እንደተለመደው እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ሜታ ኩባንያ ይህ ዜና እስከተሰናዳበት ሰዓት ድረስ ስለ አገልግሎቱ መቋረጥ ምንም አይነት ማብራሪያ አልሰጠም።

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃዎችን ሮሃ በቴሌግራም፣ በዌብሳይትና ዩቲዩብ አድራሻዋ  በተከታታይ መረጃዎችን እንደምትሰጥ መግለፅ እንወዳለን።

0 Comments

Login to join the discussion