የላስታ ወሎ አማራ ተጋድሎ

ወደመጨረሻው ድል እየተቃረብን ነው ሲሉ የላስታ አውራጃ አሳምነው ክፍለ ጦር ፋኖ አመራሮች ገለጹ

በወሎ ፋኖ ዕዝ የላስታ አውራጃ አሳምነው ክፍለ ጦር አመራሮች በአካባቢው ያለውን ትግል አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የፋኖን ወቅታዊ አቅም መጠንከርና የአገዛዙን ሃይል የሰራዊት አባላት መበታተን የተቻለበትን እንቅስቃሴ አስረድተዋል፡፡
የላስታ አውራጃ ፋኖ አሳምነው ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሀምሳ አለቃ ወንድሙ ማሩ፤ ምክትል አዛዥ  ኮማንዶ ፍቅሩ እንዲሁም የክፍለ ጦሩ ስራ አስኪያጅ ፋኖ አለምነው መብራቱ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ በአካባቢው እየተመዘገበ ያለው ተከታታይ ድል ወደ ታላቁ የድል ደጃፍ የሚወስድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የክፍለ ጦሩ ስራ አስኪያጅ ፋኖ አለምነው መብራቱ ክፍለጦሩ በአሁኑ ወቅት ላስታ፤ መቄት፤ ዳውንት፤ ግዳን፤ ላሊበላ፤ ቡግና እንዲሁም በዋግህምራ ሙሉ ዞኑ በማካለል የሚንቀሳቀስ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በዚህ ሁሉም ተሳትፎ እንዲያደርግና በመደበኛው አደረጃጀት ውስጥ እንዲካተት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ፋኖ አለምነው በወሎ ዕዝና በምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በአካል ተገኝነተን እየሰራን ነው ያለ ሲሆን ድጋፎች እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ሀምሳ አለቃ ወንድሙ ማሩ በበኩሉ የአማራውን የህልውና ተጋድሎ ለማኮላሸት አድማ ብተና ፖሊስና ቅጥረኛ ሚሊሻ አባላት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ከትዕግስትም በላይ ስለሆነ አጸፋዊ እርምጃ መውሰዳቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
መከላከያ የሚባለው ሃይል በብዛት እየተቀላቀለን ይገኛል የሚለው ዋና አዛዡ  የሁሉም ብሄሮች ፋኖ እንዲቋቋም ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሆነና ይህንንም እየገፉበት መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ምክትል አዛዡ ኮማንዶ ፍቅሩ በሰጠው መግለጫ ደግሞ ባለፉት ሰባት ወራት በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ መቻሉን በዝርዝር ያብራራ ሲሆን በክፍለ ጦሩ ውስጥ እየተቋቋሙ ስላሉ ብርጌዶችና ሻለቃዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኮማንዶ ፍቅሩ አክሎም የፋኖ ሰራዊት በወታደራዊ ስነምግባር ታንጾ የተጎዳውን ማህበረሰብ አንገት ቀና ለማድረግ የሚያደርገው ተጋድሎ መዳረሻው ኢትዮጵያ በመሆኑ ከአማራ ውጭ ያለው የአገዛዙ ሰራዊት አባላት ሳይቀሩ እየተቀላቀሏቸው መሆኑን ገልጧል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion