የአማራ ማህበራት መግለጫ

መላው አማራ ከየትኛውም መጓተት ወጥቶ ለትግሉ እንዲሰለፍና እንዲተባበር የአውሮፓ የአማራ ማኅበራት ፌደሬሽን አሳሰበ

የአማራ ማህበራት ፌደሬሽን ከአውሮፓ የጀግናው አርበኛ ውባንተ አባተን መስዋዕትነት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ለመላው አማራና ኢትዮጵያዊያን መልዕክቱን አስተላልፏል።
በእነ ጎቤ፣ በእነ አስማረ፣ በእነ ጀኔራል አሳምነው፣ የተለኮሰውን የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ፣ እነ ሻለቃ አስቻለው፣ እነ ሞላ ደስየ በእነ አይሸሽም እና የመሳሰሉት ምርጥ የዐማራ ጀግኖች ያስቀጠሉትን ትግል፣ ዛሬ ምስጋና ለእነ ሜጄር ጄኔራል ውባንተና የትግል ጓዶቹ አሁን ለደረሰበት የህልውና ትግል ከፍታ አብቅተዉታል ይላል መግለጫው።
እንዲሁም ክብርና ምስጋና የአያት ቅድመ አያቶቹ ልጅ ለሆነው እና መቼም ለማንረሳው፣ ለወንዶቹ ቁና ለፋኖ ውባንተ ይሁን ሲል ያክላል።
በጀግናችን መሰዋት ምክንያት የተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች የጀመሩት ታሪካዊ ተልዕኮ "ዘመቻ ውባንተ"ን ለበለጠ አንድነት፣ ለተሳለጠ ወታደራዊ መማከል እና የፖለቲካ ድል ለማብቃት አጋጣሚውን ይጠቀሙበት ሲልም ፌደሬሽኑ  የአክብሮት ጥሪውን አስተላልፏል።
የአውሮጳ የዐማራ ማኅበራትም "ዘመቻ ውባንተ"ን በመደገፍ የትግሉ ደጀን መሆናቸውን ያርጋግጣሉ ሲል መግለጫው አስፍሯል።
በአገር ዉስጥ ለሚገኘዉ ዐምሓራ በሙሉ መግለጫው ባቀረበው ጥሪ "የአገዛዙን አረመኔ ኃይል ማስቆምና ህግና ስርዓት ማስፈን የምትችለው የህልውናው አደጋ የተጋረጠብህ አንተው የአገሪቱ ምስሶ የሆንከው የታሪክ ባለአደራው ዐምሐራ ነህ" ብላል።
በዚህም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የአብራክህ ክፋይ የሆነውን ፋኖ በመቀላቀል እና በደጀንነት በመደገፍ የመከራና ስቃይህን ጊዜ ታሳጥረው ዘንድ ጥሪ እናደርጋለን ብሏል መግለጫው።
ፌደሬሽኑ በዓለም ዙሪያ ላሉ ዐማራውያን በሚል ባቀረበው ጥሪ ደግሞ "እንዲህ ዓይነቱን ፍትሃዊ የህልውና ትግል አለማገዝ፣ አለመቆጨትና ለወገን ድምጽ አለመሆን በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው።" ብሏል።
በውጪ ያለው የዐማራውያን ቁጥርና ለፋኖ እና ለመከረኛው ህዝብ የሚደረገው የገንዘብና የቁስ እገዛ ሲነፃፀር በእጅጉ የሚያስደነግጥ ነው ያለው መግለጫው እንዲህ ዓይነቱ ፍትሃዊ የዐምሐራ ሕዝብን ትግል ለመደገፍ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነበር ሲልም አክሏል።
ዐማራ ሆኖ እንዳላየ እንዳልሰማ መሆን ግን እጅግ በጣም አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ነው ያለው የአማራ ማህበራት ፌደሬሽኑ ስለሆነም ጠላቶችና የጠላትን ተልዕኮ ተሸክመው መሰሪ አጀንዳዎችን ለሚሰጡን ኃይሎች ቀዳዳ በመክፈት እርስ በእርስ ከመጓተት ይልቅ እንደ ጀግኖቻችን፣ ሜዳ ላይ ለመታገል ባንታደል እንኳን፣ ባለን በምንችለው፣ አቅምና መክሊታችን በሚፈቅድልን ልክ ህዝባዊ ትግሉን በማገዝ ከታሪክ ተወቃሽነት እንዳን ሲል አሳስቧል።
ዐማሓራ ላልሆናችሁ ሌሎች ወንድም እና እህት ኢትዮጵያውያን በሙሉ  በሚል በቀረበው ጥሪ ደግሞ ፈደሬሽኑ የዐምሐራ የህልውና ትግል ስርነቀል ስርዓታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል የሚደረግ ትግል መሆኑን በማመን አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቋል።

0 Comments

Login to join the discussion