ከብልጽግና እጅ እየወጣች ያለችው ጎንደር
የጎንደር በርካታ አካባቢዎች በዘመቻ ውባንተ በፋኖ እጅ መግባታቸው ተነገረ
ታላቁ ታጋይ ሜጀር ጀነራል ውባንተ አባተን መሰዋት አስመልክቶ በሁሉም የአማራ ግዛቶች በታወጀው ዘመቻ ሁሉም የአማራ ልጆች ታላላቅ ድሎችን እያስመዘገቡ ነው፡፡
በጎጃም ፣ በወሎና በሸዋ የነበሩ የዘመቻ ውባንተ ድሎችን ላለፉት ቀናት በስፋት ስናነሳ የነበረ ሲሆን ፣ በዚህም ፋኖ በምርኮ ፣ በወዶ ገብና በግዳይ መንበሽበሹን ከአውደ ውጊያ የደረሱንን መረጃዎች ዋቢ አድርገን ስንዘግብ ቆይተናል፡፡
አሁን ደግሞ በሁሉም የጎንደር አካባቢዎች በዘመቻ ውባንተ በተካሄዱ ተጋድሎዎች ፋኖ የብልጽግናውን አገዛዝ ቅስም የሚሰብሩ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡
በጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደው በዚህ ዘመቻ ፋኖ ብልጽግና ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል፡፡
በፋኖ ሲሳይ አሸብር የሚመራው የአርማጭሆ ፋኖ የአገዛዙ ወታደር ሰፍሮባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ይዟል፡፡
በተመሳሳይ በሻለቃ ደረጄ በላይ የሚመራው ፋኖም ደንቢያን የተቆጣጠረ ሲሆን ፣ የአድማ ብተና እና ሚሊሻም ደንቢያን ለቋል ፣ የተቀረውም ለፋኖ እጁን ሰጥቶ ተደባልቋል፡፡
በአርበኛ መሳፍንት የሚመራው ፋኖም በዳባት ፣ በአጅሬ ፣ ጃኖራና በሌሎች በሰሜን ጎንደር ያሉ አካባቢዎችን ከአገዛዙ አጽድቶ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡
ከባድ ትንቅንቅ እየተካሄደበት ያለው የደቡብ ጎንደር አካባቢ በበለሳ ፣ በእብናት ፣ በጉና በጌምድር እና በሌሎች አካባቢዎች የጣይቱ ክፍለጦር አንድ ሻለቃ ሙሉ በሙሉ ማርኳል ፣ ክምር ድንጋይና አካባቢውንም ተቆጣጥሯል፡፡
ታች ጋይንትና ላይ ጋይንትም አብዛኛው አካባቢ በፋኖ እጅ ገብቷል፡፡ አርበኛ ውባንተ የተሰዋባት ገላዲዎስ ከተማም በፋኖ እጅ ገብታለች፡፡ የደራ ሃሙሲት ዋና ከተማም ከአገዛዙ ነጻ ሆና በልጆቿ እጅ ናት ተብሏል፡፡
ይህም በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ የጎንደር አካባቢዎች በፋኖ እጅ የገቡበት ክስተት ሆኗል፡፡
ዘመቻ ውባንተን አስመልክቶ ምላሽ የሰጠው የአማራ ፋኖ በጎንደር እዝ ዋና አዛዥ ሻለቃ ሃብቴ ወልዴ ፣ በዘመቻው ታላላቅ ድሎችን አግኝተናል ብሏል፡፡
ሻለቃው ዘመቻው የጎንደርን ትግል አንድ ደረጃ ከፍ አድርጓል ያለ ሲሆን ፣ ሜጀር ጀነራል ውባንተ በታላቅ ጀብዱ ተሰውቷል ሲልም ተናግሯል፡፡
ሻለቃ ሃብቴ ወልዴ በዘመቻ ውባንተ በርካታ የቡድን መሳሪያዎችን አግኝተናል ፣ የአገዛዙ ጦር አይቀጡ ቅጣት ቀጥተንበታል ሲልም አስታውቋል፡፡ የብልጽግና ጦር እጅ ለመስጠት እንኳን ጊዜ እንዳያገኝ ያደረግንበት ነውም ብሏል፡፡
ከፈራረሰው የአገዛዙ ሃይል አንጻርም በቅርቡ ታላቅ ብስራት ይኖረናል ይላል የፋኖ አዛዡ፡፡
Login to join the discussion