ወጣቱ የግፍ አስረኛ

የአዲስ አበባው ታጋይ ናትናኤል ያለምዘውድ ወደ አዋሽ አርባ ተወሰደ

የባልደራስ ፓርቲ የስራአስፈፃሚ አባል እና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ናትናኤል ያለምዘውድ ከአራት ቀናት በፊት በኦህዴድ-ብልፅግና ሀይሎች ከመኖሪያ ቤቱ ታፍነው መወሰዱ ይታወሳል።
ይህንኑ በማስመልከት ፓርቲው ባልደራስ ዛሬ በሰጠው አጭር መግለጫ ናትናኤል ከታፈነበት ቀን ጀምሮ ፍ/ቤት አለመቅረቡንና እና በቀጨኔ ፖሊስ ጣቢያ በግፍ እስር ላይ ይገኝ እንደነበር ጠቅሷል።
ከዚያም በኋላ ፖሊስ የግፍ እስረኛውን ከቀጨኔ ፖሊስ ጣቢያ አውጥቶ ወደ ላዛሪስት ፖሊስ ማዘዣ ወስዶት እንደነበር ታውቋል።
ትናንት ሰኞ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም የግፍ እስረኛው ቤተሰቦች፣ አቶ ናትናኤል በግፍ እስር ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ከ72 ሰአታት በላይ ፍ/ቤት አለመቅረቡን አጣቅሰው፣ አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታ አቅርበው እንደነበርም ባልደራስ አስታውቋል።
ነገር ግን የፍ/ቤትን መልስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ዛሬ ለሊት አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱ ታውቋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የግፍ እስረኛውን አስመልክቶ ለሚመለከታቸው አካላት ተፅእኖ እንዲያደርጉ በትላንትናው እለት ደብዳቤ ፅፎ እንደነበርም ተገልጿል።
ባልደራስ በመግለጫው ላይ አቶ ናትናኤል ላይ እየደረሰ ያለውን በደል አጥብቆ እንደሚያወግዝ ያስታወቀ ሲሆን፣ አገዛዙ የግፍ እስረኛውን በአስቸኳይ እንዲፈታ አሳስቧል።
ናትናኤል ያለምዘውድ አዲስ አበባ ላይ በሚደረጉ የህዝብ መብት ትግሎች ላይ በመሳተፉ በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገ ሲሆን በተለይም የብልፅግና አገዛዝ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ለቁጥር በሚያዳግት ሁኔታ ናትናኤል ደጋግሞ አፍኖታል።
ሰሞኑንም አዲስ አበባ ውስጥ ተቃውሞ ይነሳል በሚል ፍርሃት ከቀናት በፊት ናትናኤልን በኮማንድ ፖስት ስም ያፈነው ብልፅግና ዛሬ ደግሞ የግፍ እስረኞች ማሰቃያ ቦታ ወደሆነው አዋሽ አርባ ማጎሪያ ካምፕ ወስዶታል።
ሮሃ በተደጋጋሚ እንደዘገበችው በአሁኑ ወቅት በአዋሽ አርባ ታጉረው የሚገኙ ጠበቃ አዲሱ ጌታነህና ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ጨምሮ የአማራ ተወላጆች በአዋሽ አርባ የሚፈፀምባቸው ማሰቃየት መባባሱ ይታወቃል።

0 Comments

Login to join the discussion