የጎንደር አካባቢዎች ውጊያ

ጎንደር ከተማን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ውጊያና የደፈጣ ጥቃቶች እየተካሄዱ ነው
በማዕከላዊ ጎንደር ደንቢያና አካባቢዋ ላይ ከባድ የሚባል ውጊያ ከሰሞኑ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአካባቢው የብልጽግና ሃይልም ከፍተኛ የተባለ ወታደራዊ ሃይል እያስገባ ነው ተብሏል፡፡
በተለይም በደንቢያ በር ፣ በቆላድባ ሮቢትና በጠዳ ሃምሳ ፈጅ አካባቢዎች ነው ውጥረቱ ያየለው፡፡ ይህም ብልጽግና በደንቢያ ፋኖን አጸዳለሁ በሚል ውጊያ ለመክፈት በማሰብ ያደረገው እንቅስቃሴ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከሰሞኑ በደንቢያ አካባቢዎች በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ውጊያዎች ወታደሮቹ ሙትና ቁስለኛ ሆነውበት የተሸነፈው ብልጽግና በርካታ ሃይል አሰልፎ ወደ አካባቢው መግባቱ ነው የተነገረው፡፡
ይሁን እንጂ የፋኖ ሃይሎች በተጠንቀቅ ቆመዋል ተብሏል፡፡
በዚሁ በደንቢያ ሮቢት አካባቢ ገበሬዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እየተደረገ ሲሆን ፣ በዚህም በአካባቢው ተጨማሪ ከባድ ውጥረት ነግሷል፡፡
በሌላ በኩል  በጎንደር ከተማ ጠዳ ክፍለ ከተማ እርሻ ኮሌጅ አካባቢ በሰፈሩ የሚሊሻ ሃይሎች ላይ በፋኖ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በእርምጃውም ከ5 በላይ ሚሊሻዎች ሲገደሉ ፣ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
በጎንደር ከተማ አዘዞ ክፍለ ከተማም አጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ላይ ትናንት ማምሻውን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በነበሩ የፌደራል ፖኦሊስ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል፡፡
በተጨማሪም ከጎንደር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ማክሰኚት ከተማ የፖሊስ ስምሪት ሃላፊ በፋኖ ጥቃት ተፈጽሞበት ጎንደር ሆስፒታል ገብቷል፡፡
ከጎንደር ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃ ደግሞ በአርማጭሆና በጠገዴ ውጊያዎች እየተካሄድ ነው፡፡
በታች አርማጭሆ ማሰሮ ደም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን እስከ ቀትር ድረስ ውጊያው መቀጠሉም ነው የታወቀው፡፡
በጠገዴ ወረዳ ቅራቅር ከተማም የፋኖ ሃይሎች የገቡ ሲሆን ፣ ይህ ቦታም የወልቃይት አዋሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በከተማዋም ፋኖ ሲገባ ህዝቡ በደስታ ተቀብሎታል፡፡ ፋኖ ወደ ከተማዋ የገባው ከዚህ በፊት የፋኖ አባል የነበረ ግለሰብ መሳሪያዎችን ይዞ ለወረዳው የብልጽግና ሰዎች በማስረከቡ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያ ፋኖ ወደ ከተማዋ በመግባትና ከተማዋን በመቆጣጠር መትረየስን ጨምሮ የተወሰደበትን መሳሪያ አስመልሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ጎንደር ጋሳይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በዛሬው እለት ለሁለት ሰዓታት የቆየ ውጊያ መካሄዱ ተሰምቷል፡፡ በአካባቢው መከላከያ ሰራዊቱ ካምፕ ለመመስረት ባደረገው እንቅስቃሴ የተጀመረው ይህ ውጊያ በፋኖ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የብልጽግና ጦርም ያሰበውን ካምፕ ሳይመሰርት ስፍራውን ለቆ ወጥቷል፡፡
በሌላኛው የደቡብ ጎንደር አካባቢ ሙጃ ቀበሌ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡ በውጊያውም ከ15 በላይ የብልጽግና ወታደር መገደሉ ታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎም ተጨማሪ ሃይል ያስገባው አገዛዙ አርሶ አደሮችን ፋኖን ትረዳላችሁ በሚል እየገደለ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡ ውጊያው አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ በደቡብ ጎንደር ጉና ተራራ አቅራቢያ አምጃዬ በተባለች ስፍራ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በፋኖ እና በብልጽግና ጦር መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡

0 Comments

Login to join the discussion