የአማራ ፋኖ ወሎ እዝ ጥሪ

የአማራ ፋኖ ወሎ እዝ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የሰብዓዊ ድጋፍ ጥሪ ቀረበ

በድሮ ሥም አጠራር በግዙፉ የምሥራቅ ዐማራ ፋኖ ዕዝ እና በዐማራ ፋኖ ወሎ ዕዝ መካከል በብዙ ፈተናዎች ታጅቦ ሲደረግ የነበረው ምክክርና ውይይት ፍሬ አፍርቶ በተገኘው የአንድነት ውህደትን ተከትሎ ዕዙ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ነገር ግን አዲስ የተፈጠረው ውህደት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች እና ሌሎቹ መዋቅሮቹ በሙሉ ተሰርተው አልቀው በሙሉ አቅም ስራ እስኪጀምር ድረስ ወሎ ዕዝ ሲንቀሳቀስበት በነበረው ቀጠና አስቸኳይ ጊዜ የማይሰጥ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም የአማራ ፋኖ ወሎ ዕዝ በተቆጣጠራቸውና በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች በጦርነቱ ሠለባ ለሆኑ ሠብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ለደረሠባቸው የህብረተሠብ ክፍሎች የሚውል ዓለም አቀፍ የእርዳታ ጥሪ እዙ አቅርቧል፡፡
እዙ የስርዓቱን አስከፊነት በመቃወም ብዙ ዋጋ በከፈሉ እና እየከፈሉ ባሉ ጥቂት ቆራጥ አንጋፋ መሪዎች ከአዲሱ የበቃ እና የተማረ ተስፋ ካለው የአማራ ወጣት ጋር ተቀናጅቶ ወደ ትግል የገባ የአማራ ፋኖ ዕዝ መሆኑም ተነስቷል።
የአማራ ፋኖ ወሎ ዕዝ በልዩ ዞን ሽፋን ሠሜን ኦሮምያን ለመመሥረት በሚናፍቁ እና ቆርጠው ከሚሠሩ፣ እንዲሁም መንግስት መራሽ የኃይማኖት ፅንፍ ባላቸውና  በሙስሊምነቷ እዝነት ሳያሳዩ በዐማራነቷ ወለጋ ውስጥ አንሻ ሠይድን አርደው ያልረኩ ኃይሎች በሚራወጡበት ቀጠና የሚንቀሳቀስ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሁለት ቀደምት እምነቶች የፀና መንፈሳዊ  የተሠናሠነ ማንነት ባለው ህዝብ መሀል ግጭት ጠማቂው መንግስት የግጭት ካርዶችን በሚመዝበት ቀጠና በመንቀሳቀስ የአብይ የኃይማኖት ሴራን ያከሸፈ ትልቅ አደረጃጀት ያለው ዕዝ እንደሆነም በመግለጫው ተነስቷል።
ወሎ ዕዝ ከዋግ ኽምራ አስከ ምድረገኝ ኬሚሴ እና ከአራቱም ክፍላተ ሀገራት ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር አዋሳኝ የጦር ግንባሮችን በመፍጠር ጠላትን ማጥቃት የሚችል ሠፊ የፋኖ ሠራዊት አሠማርቶ በመታገል ብዙ ጀብዱ እየሠራ የሚገኝ ሠፊ አደረጃጀት ነው።
በመሆኑም ወሎ ዕዝ ከአገዛዙ የሚመጣን ፍላፃ በመመከትና በመልሶ ማጥቃት በደፈጣና በመደበኛ ውጊያ ኪሳራ ያደረሰበት የአገዛዙ ጦር በህዝቡ ላይ በነፍስ ወከፍ መሳሪያ ከሚፈፅመው ግድያ ባሻገር በከባድ መሣሪያና በድሮን የአርሶ አደር ሰብል ወድሟል፣ በሁለት አመቱ የህወሃት ዝርፊያና ወረራ የተረፈው የነጋዴዎች ወረት ተዘርፏል፣ ጤና ተቋማት እና አምቡላንሶቻቸው በድሮን እንዲወድሙ ተደርጓል።
“ስለሆነም ይህንን ማህበረሠብ በጠላትነት የፈረጁት ኃይሎች እየተፈራረቁ ካደረሱበት ዘርፈ ብዙ ችግር ለጊዜው ለማስታገስ ካለንበት ውስብስብ ቀጠናዊ ተግዳሮት አንፃር በይፋ እርዳታ ሳንጠይቅ ቆይተናል” ይላል መግለጫው።
ስለሆነም በውጭ ሀገር የሚኖር አማራ በምናደርገው የህልውና ትግል ውስጥ ከሀሳብ እስከ ፋይናንስ በማገዝ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በመሆኑም የወሎ ዕዝ ፋኖ በውጭ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን እና ሌሎች የፋኖን እንቅስቃሴ ደጋፊዎችን በማስተባበር እና የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በማሰብ በዕዙ የበላይ አመራር ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ የውጭ ማህበረሰባችንን በማስተባበር አስቸኳይ እና ጊዜያዊ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን በኮሚቴው በኩል ላለፉት አስር ያህል ቀናቶች ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ኮሚቴውም አስር አባላት ያሉት ሲሆን አቶ መሐመድ ሊበንም የኮሚቴው ሰብሳቢ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ገኒ የማርያም ልጅ ፣ እሱባለው ደጉ ፣ ወርቅዬ በላይነህ ፣ የቦረናው ዘማች ፣ ስመኘው እና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ አራት ሰዎች በኮሚቴው ተካተዋል።
“ስለሆነም በውጭ የምትኖሩ የአማራ  ባለሀብቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ዩቱዩበሮች፣ ቲክታከሮችና በሁሉም የሚዲያ ፕላትፎርሞች ውስጥ ያላችሁና የፋኖን የህልውና ትግል የምትደግፉ ወገኖቻችን ትብብራችሁን የምንጠይቅ መሆኑን እየገለጽን እናንተ በምትሳተፉባቸው ሚዲያዎች ያሉትን አድማጭ-ተመልካቾቻችሁን፣ አድናቂዎቻችሁንና ደጋፊዎቻችሁን ግንዛቤ በመፍጠር በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት አራትና አምስት እንዲሁም ግንቦት 11 እና 12 ለሚደረገው ዘመቻ የበኩላችሁን አሻራ እንድታሳርፉ” ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተለያዩ የአለም ክፍሎች ላሉ 51 ገደማ የአማራ ማህበራትም የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion