የአማራ ፋኖ መግለጫ

የአማራ ፋኖዎች የትንሳኤ በዓልን በሚመለከት የጋራ መግለጫ ሰጡ
የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ በሁሉም ግዛቶች ያሉ የፋኖ አደረጃጀቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡
የአማራ ፋኖ በጎጃም በጦር አዛዡ ሻለቃ ዝናቡ ልንገረው በኩል በትናንትናው እለት ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የአማራ ህዝብና ፋኖ አገዛዙ በዓልን አስታኮ ከሚፈጽመው የአየር ጥቃት እንዲጠነቀቁ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ የፋኖ አባላት በዓሉን ከተቸገረው ወገናቸው ጋር ያላቸውን አካፍለው እንዲያከብሩ አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ በዛሬው እለት የአማራ ፋኖ ጎንደር እዝ ዋና አዛዥ ሻለቃ ሃብቴ ወልዴ ባስተላለፈው መልዕክት “እጅግ አስቸጋሪ በሆነ የሕልውና ትግል ውስጥ ብንሆንም በራሴ እና የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ስም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሳኤ በዓል በጽናት አደረሰን፤ አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ” ብሏል፡፡
በመልዕክቱም “የአማራ ፋኖ የገባበት የህልውና ትግል፣ ብአዴን-ብልጽግና በተባለ የዘመናችን አስቆረቱ ይሁዳ ክህደት የተነሳ ለዘመናት የመስዋዕት በግ ሆኖ የቀረበውን የአማራ ሕዝብ ከታወጃበት የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት በክንዳችን ለመታደግ ነው” ሲል አስፍሯል፡፡
ከትንሳኤው በር ለመድረስ ሰሞነ ሕማማትን ማለፍ ግድ እንደሆነው ሁሉ አማራ ወደማይቀረው ድል ከመድረሱ በፊት የመከራውን ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በፈተናው የበረታ የጨለማውን ጊዜ ያልፈዋል፤ ሕማማቱን የጸና የትንሳኤውን ብርሃን ያየዋል ሲልም አክሏል፡፡
ትግላችን የቱንም ያህል ፈታኝና መራራ ቢሆንም በሞት ሸለቆ ሳይታለፍ ታሪክ አይቀየርምና ለአማራ ትንሳኤ የማይተካ ሕይወታችንን ዋጋ እየከፈልን የአማራ ሕዝብን ትንሳኤ በመስዋዕትነታችን እናረጋግጠዋለን ያለው አዛዡ የትንሳኤ በዓል በአብሮነት የሚከበር በዓል በመሆኑ ካለንበት ወቅታዊ የትግል ሁኔታ አኳያ በዓሉን ስናከብር በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
በተጨማሪም ለድሮን ጥቃት ተጋላጭ ሊያደርጉን ከሚችሉ መሰባሰቦችና የተጋላጭነት ሁኔታን የሚያሳድጉ ሁነቶችን ከመፍጠር ተቆጥበን፣ በተለመደው የመረዳዳት መንፈስ እንዲከበር ለሕዝባችን የአደራ መልዕክት አስተላለፋለሁ ሲል ቋጭቷል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ፋኖ በጎንደር ዋና አዛዥ አርበኛ ባዬ ቀናው ባስተላለፈው መልዕክት “ በቤተ እምነት፣ በድግስና በገበያ አካባቢዎች ተሰባስቦ ማክበር ለድሮን ጥቃት ኢላማነት ስለሚያጋልጥ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ይህንን ባለማድረግ የራሱን ደህንነት መጠበቅ እንዲችል” ብሏል፡፡
“በገበያና በእምነት ቦታዎች ዙሪያ የማህበረሰቡን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ጸጉረ ልውጦችን በአትኩሮት በመከታተል በተለይ ወጣቶች ይህንን በማድረግ የማህበረሰቡንና የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሀላፊነት እንድትወስዱ” ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
“በድግስ፣ የደስታ ወይም የሀዘን መግለጫ ቦታዎች ላይ ወይንም ማንኛውም ሰላማዊ ሰዎች በተሰበሰቡበት አካባቢ ምንም አይነት ተኩስ እንዳይኖር፤ ይህንን ተላልፎ ህገወጥ ድርጊት የሚያደርግ አካል ካለ በአካባቢው ላሉ የፋኖ አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲደረግ” ሲልም አሳስቧል፡፡
“በአልን ተገን በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በሀሰት የፋኖ አባላት በመምሰል የዝርፊያ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦችን በመለየት ለማህበረሰቡ ብሎም በአካባቢው ላሉ ለትክክለኛ የፋኖ አባላት አጋልጦ በመስጠት እንድትተባበሩ” ይላል በመልዕክቱ፡፡
በተጨማሪም የአማራ ፋኖ ወሎ እዝ ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃም ፣ የአማራ ፋኖ ሸዋ እዝ እና የአማራ ፋኖ በጎንደር በጋራ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም “ህዝባዊ ትግሉን በተለያየ መንገድ እያገዛችሁ ሲደክመን እያበረታታችሁ፣ ስንሳሳት እያረማችሁ ያላችሁ መላው የአማራ ህዝብና የትግሉን እውነተኛነት በዉል የተረዳችሁ በየትኛውም አካባቢ የምትገኙ ማህበረሰባችን ትግላችን ተገፍተን፣ ተበድለን፣ ችለን፣ ታግሰን፣ ተናግረን፣ ጮኸን ሰሚ አጥተን የጀመርነው ትግል እንጂ የፀብ አጫሪነት ትግል አለመሆኑን በመረዳት የጀመራችሁትን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የግፍ ሞት በታወጀበት የአማራ ህዝብ ስም መልዕክታችንን እናስተላልፋለን” ብለዋል።

0 Comments

Login to join the discussion