የዐቢይ የባህርዳር ጉዞና ፋኖ

ማምሻውን በባህርዳር ጥቃት የፈጸመው የአማራ ፋኖ በጎጃም የዐቢይን ወደ ባህርዳር መምጣት በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑን ገለጸ
የጨፍጫፊው አገዛዝ ዋና መሪና በአገሪቱ የሚደረጉ የግፍ ግድያዎች ዋነኛ አቃጅና አስተግባሪ አብይ አህመድ አሊ በገፍና በግፍ ወደ ሚያስጨፈጭፉት የአማራ ህዝብ ዋና መቀመጫ ባህርዳር ሊያቀኑ መሆኑ ታውቋል፡፡
የጉዟቸው አላማ ደግሞ አማራን እየጨፈጨፉ ለመሳለቂያ ይሆን ዘንድ የተሰሩትን የጎርጎራ ፓርክና የአባይ ድልድይ ለማስመረቅ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡
ጉዟቸውም ዛሬ ቅዳሜ አሊያም ነገ እሁድ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ የጉዟቸው ዋነኛ አላማም ወደ ነቀምት ተጉዘው ወለጋ ሰላም ነው እንዳሉት ሁሉ ወደ ባህርዳር አቅንተው አማራ ክልል አማን ነው ለማለት እንደሆነ ታውቋል፡፡
ታዲያ ይህ የስላቅ ጉዟቸው እውን እንዳይሆን እሰራለሁ ሲል የአማራ ፋኖ በጎጃም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ፋኖ ሰውዬው ወደ ባህርዳር ጉዞ የሚያደርጉ ከሆነ አስፈላጊውን እርምጃ እወስዳለሁ ያለ ሲሆን ማስጠንቀቂያ ይሆን ዘንድም በትናንትናው እለት በከተማዋ አምስት አካባቢዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል፡፡
የአማራ ፋኖ በጎጃም የ1ኛ ክፍለጦር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፋኖ ሙሉሰው ለአንከር ሚዲያ እንደገለጹት “ ዐቢይ ወደ ባህርዳር እመጣለሁ በማለቱ የማስጠንቀቂያ እርምጃ ወስድናል” ብሏል፡፡
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከልም የአገዛዙን ፕርፓጋንዳ ከሚያስተላልፉት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን /አሚኮ / ነው፡፡
በተጨማሪም ዐቢይ በሚመጡበት ወቅት እርምጃ እንደሚወስድም ጠቁሟል፡፡በተጨማሪም በትናንት ምሽት በተፈጸመው ጥቃት ዝርዝር ጉዳቱን ማወቅ አልቻልንም ያለው ቃል አቀባዩ ፣ በአሚኮ ላይ ጉዳት መድረሱን ግን አንስቷል፡፡
ዐቢይ ህዝቡን ለማደናገርና የውሸት ፕርፓጋንዳ ለመንዛት ነው የሚመጣው ያለው ፋኖ ሙሉሰው የዐቢይን መምጣት የአማራ ፋኖ በጎጃም በተጠንቀቅና በጉጉት  እየጠበቀ ነው ሲል ገልጿል፡፡
ነገር ግን ከአበባ ሻጭ ጀምሮ ለመቀበል ሽር ጉድ የሚሉ አካላት ቢጠነቀቁ ይሻላቸዋል ብሏል፡፡


0 Comments

Login to join the discussion