የፋኖ ምላሽ ስለዐቢይ ጥሪና ድርድር !
ፋኖ “ከዐቢይ ጋር ድርድር የምናደርገው ሰውዬው ከአገር ሲነቀል ብቻ ነው” ሲል ለባህርዳሩ ጥሪ ምላሽ ሰጠ
የአማራን ህዝብ በተለያዩ አቅጣጫዎች እያስጨፈጨፈና እየጨፈጨፈ የከረመው ዐቢይ አህመድ አሊ ከትናንት በስቲያ ወደ ሚጨፈጭፈው ህዝብ ዋና ከተማ ባህርዳር አቅንቶ የለመደውንና ህዝብን የናቀ ስላቅ ተሳልቋል፡፡
ሰውዬው በንግግሩ “ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ተመልሷል እነሆ አረጋ ከበደ ተሹሞለታል” ሲልም የአማራ ትግል አረጋ ከበደን ለማንገስ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ማንነታችንን መሰረት ያደረገ ግድያ ፣ መፈናቀል ፣ መሰደድ አንሻም ፣ ተከብሮ መኖር ፣ ሰርቶ ማደር ፣ ተምሮ መለወጥ ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ነው ጥያቄያችን ሲል በሰላም የጠየቀው የአማራ ህዝብ ፣ መልሱ ሹፈት ሲሆንበት ሰልፉን በሰይፍ ቀይሮ ክንዱን እያሳየ ነው፡፡
ታዲያ አብይ በባህርዳር ጉዞው ፋኖ ከአረጋ ከበደ በታች ሆኖ ይስራ በሚል ስላቅ ፣ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምትሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህ ጨፍጫፊና ገዳይ ስርዓት በመሪው በኩል ባስተላለፈው የይምሰል ንግግር ዙሪያም የፋኖ አመራሮች ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
ፋኖዎቹም ንግግር የምናደርገው ዐቢይንና ስርዓቱን አስወግደን ነው እያሉ ነው፡፡ የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት እዝ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፋኖ አበበ ሙላት በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ግለሰብ እንጂ መንግስት አይደለም ብሏል፡፡ “እኛም ነፍጠኞች ነን ነፍጠኛ እያሉ ሊያሳቅቁን አይሞክሩ” ሲል አስታውቋል፡፡
“ዐቢይ በአሁኑ ሰዓት እንደራደር ፣ አብረን እንስራ የሚል ፖለቲካ ነው እየሰራ ያለው” የሚለው የፋኖ ቃል አቀባዩ ፣ “ከጨፍጫፊና ፣ ከዘራፊ ቡድን ጋር ፈጽሞ አንደራደርም” ሲል አስታውቋል፡፡ “ከዐቢይ ጋር የምንደራደረው ምኒሊክ ቤተመንግስት በር ላይ ያቆማትን ወፍ ይዞ ከአገር ሲለቅ ነው “ሲል ቅድመ ሁኔታው ምን እንደሆነ ለኤቢሲ በሰጠው ቃል ግልጽ አድርጓል፡፡
“በተጨማሪም በአማራው ላይ ለማላገጥ ባህርዳር ገብቶ የነበረው ዐቢይ ከፋኖ ጥቃት ለጥቂት ነው የተረፈው” ያለ ሲሆን ፣ “ሌሎች ህዝቦችም በጋራ ሆነው ይህን አገዛዝ ለመጣል በሚደረገው ትግል ሊሳተፉ ይገባል” ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
Login to join the discussion