የአማራ ፋኖ በጎንደር ድሎች
በጎንደር ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን ከአስራ አምስት በላይ በሚሆኑ አውደ ግንባሮች ከፍተኛ ውጊያ ተደረገ
በጎንደር ግዛት በርካታ አካባቢዎች ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 10/2016 ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች የአማራ ፋኖ በጎንደር ሰራዊት በአገዛዙ ቡድን ታጣቂ ሃይል ላይ ድልን ተቀዳጅነተዋል፡፡
በጎንደር ግዛት ከአስራ አምስት በላይ በሚሆኑ አውደ ግንባሮች ከፍተኛ ውጊያዎች መካሄዳቸውንና ይህ ክስተት ከዚህ በፊት በአንድ ቀን ከሚደረጉ ውጊያዎች ከፍተኛና የመጀመሪያ መሆኑን ሮሃ ከፋኖ አመራሮች ሰምታለች፡፡
በፋኖ ቁጥጥር ስር በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች አለኝ የሚለውን ጦር አሰልፎ ጥቃት ለመክፈት የሞከረው የብልጽግና ጦር ጦርነቱ የተገላቢጦሽ ሆኖበት መደበኛ ሰራዊቱን ብቻ ሳይሆን ጦር አዛዦቹን ሳይቀር በፋኖ እርምጃ አጥቷል፡፡
በደቡብ ጎንደር በላይ ጋይንት በጣራ ፣ ሞሰቢት ጎራ፣ ነፋስ መውጫ እና አካባቢው እንዲሁም በእስቴ፤ በደራ ገላውዲዮስና ልጫ፤ በጉና ቤጌምድር ክምር ድንጋይ፣አርባ ምንጭ ቀበሌን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የብርሃኑ ጁላ ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ በመሆኑ ከጥቅም ውጭ ተደርጓል፡፡
የአማራ ፋኖ በጎንደር ዘመቻ መምሪያ ሀላፊና የገብርየ ክፍለ ጦር አዛዥ ሻለቃ ከፍያለው ደሴ ስለ ውጊያው ሲገልጽ "የመንግስት ኃይል ከአራት አቅጣጫ ከበባ በማድረግ ውጊያ ከፈተብን። እኛም የመሬቱን አቀማመጥ መሠረት በማድረግ የኃይል ስምሪት አድርገን የተከፈተብንን ጥቃት ሙሉ በሙሉ መክተናል።›› ብሏል፡፡
አርበኛው አክሎም ‹‹በአፀፋዊ ምላሽ በመንግሥት ኃይል ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰናል። እስከ አሁን ባለው የዘጠኝ ሰዓታት ውጊያ ከዘጠና አምስት በላይ የመንግሥት ኃይል ተገድሏል።›› ሲልም ሁኔታውን ገልጾታል፡፡
የአማራ ፋኖ በጎንደር ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፋኖ ኢያሱ አባተ ከግንባር በበኩሉ በስልክ በሰጠው ቃል ከትናንቱና ከዛሬው የድል መረጃ አስቀድሞ ሰሞኑን የተሰሩ ጀብዱዎችን ጠቅሷል፡፡
Login to join the discussion