የአማራ ፋኖ በጎንደር ድል

በጎንደር ግዛት ሳምንት በሞላው መጠነ ሰፊ ውጊያ የአማራ ፋኖ በጎንደር ሰራዊት በከፍተኛ ድል መገስገሱን ቀጥሏል

በጎንደር ግዛት የተለያዩ ግንባሮች ላለፉት ሰባት ቀናት ገደማ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ባለው ውጊያ በፋኖ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለመክፈት ልዩ ዝግጅት ሲያደርግ የከረመው የብልፅግና ቡድን ሰራዊት ያልተጠበቀውና ያልገመተው ሽንፈት ገጥሞታል።

በጎንደር ግዛት የቀጠለውን ውጊያ ጨለማ ብቻ የሚከልለው የሙሉ ቀን ጦርነት መሆኑንም ሮሃ ከፋኖ አመራሮች አረጋግጣለች።

ውጊያውንና የፋኖን ከፍተኛ ድል አስመልክቶ ለሮሃ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጠው የአማራ ፋኖ በጎንደር የህዝብ ፋኖ ኢያሱ አባተ እጅግ የሚያስደንቁ ጀብዱዎች በፋኖ ሰራዊት እየተፈፀሙ መሆኑን በስልክ ነግሮናል።

ከፍተኛ ድል የተገኘበትና ሰባተኛ ቀኑን የያዘው ተጋድሎ የአማራ ፋኖ በጎንደር በጉና ክፍለ ጦር እንዲሁም በሜጀር ጀነራል ውባንተ አባተ ተወርዋሪ ክፍለ ጦርን ጨምሮ በተለያየ አደረጃጀት ስር ባሉ የፋኖ ተዋጊዎች ከባድ ትንቅንቅ መካሄዱን ቀጥሏል።

በገላውዲዮዎስ ከተማና አዋሳኝ አካባቢው በናሁሰናይ ብርጌድና ተስፋየነው ቢራራ ብርጌድ እንዲሁም ሜጀር ጀነራል ውባንተ አባተ የተሰዋበት ውባንተ ተራራ ላይ የተፈፀመው ገድል ታሪካዊ የሚባል እንደሆነ ፋኖ ኢያሱ ይገልፃል።

የአገዛዙ ጦር በተወሰደበት እርምጃ ገላውዲዮስ ከተማን ለቆ ሲወጣ  አርብ ገበያም መግባት እንዳልቻለና ወደ ማህደረ ማርያም አቅጣጫ በየተራራው መበታተኑንም ፋኖ ኢያሱ ገልፆልናል።

ቡድኑ ከተበተነ በኋላ መምሸቱንና መተያየት እንዳልተቻለ የገለፀው ኃላፊው በመምሸቱ የአገዛዙን ጦር ሙትና ቁስለኛ ቁጥር በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለና ገበሬውን የተወሰነውን እየቀበረ እንደነበር አስረድቷል።

የምርኮኛ አያያዝንና የምህረት አዋጅን በተመለከተ የአማራ ፋኖ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ፋኖ ኢያሱ አባተ በሰጠው ምላሽ ምርኮኞችን ወደ ቤተሰቦቻቸው መላክና ፋኖን መቀላቀል የፈለጉትን የመቀበል ሂደቱ መቀጠሉን ተናግሯል።

መከላከያ በሚል ስም በሶስት ወር ደካማ ስልጠና ወደ ውጊያ የሚላኩ የአገዛዙ ወታደሮችን አዛዦቻቸው እጅ ከሰጣችሁ በአሰቃቂ ሁኔታ ትገደላላችሁ ስለሚሏቸው በተሳሳተ አረዳድ በውጊያው እንደሚሞቱ አስረድቷል።

ይህንንም ከምርኮኞች ማረጋገጥ እንደተቻለ እና ፋኖ ግን ከሚባለው በተቃራኒ ቁስለኛ ምርኮኞችን በእኩል ደረጃ በማሳከም ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ወደ ቤተሰቦቻቸው እስከመሸኘት መድረሱን ፋኖ ኢያሱ አረጋግጧል።

ለምርኮኞች ደህንነት ሲባል በቪዲዮ ይፋ የማይሆኑ ነገሮች በመረጃ ፍሰቱ ላይ ስለፈጠሩት እንቅፋትም ኃላፊው ያስረዳል።

0 Comments

Login to join the discussion