የተራዘመው የምህረት አዋጅ

የአማራ ፋኖ በጎንደር ለአገዛዙ የጸጥታ ሃይሎችና ለታችኛው መዋቅር አመራሮች የሰጠውን የምህረት አዋጅ አራዘመ
የአማራ ፋኖ በጎንደር ለጸጥታና የታችኛው መዋቅር አካላት ያወጣው የምህረት አዋጅ ከግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የምህረት አዋጁ ጠቀሜታ ላቅ ያለ ሆኖ በመገኘቱ ሳቢያ ለተጨማሪ 15 ቀናት ማለትም ከዛሬ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲራዘም ወስኗል፡፡
“የአድማ ብተና፣ ሚሊሻ፣ ህዝባዊ ፖሊስ (አማራ ፖሊስ)፣ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ መረጃና ደህንነት አባላት እንዲሁም የታችኛው መዋቅር የአገዛዙ አካላት በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት አውጆ ህዝብ እየጨፈጨፈ፣ ቤት ንብረት እያወደመ፣ እንስሳትን እየገደለና የአማራን ህዝብ በቃላት ሊነገር የማይችል ሰቆቃ ውስጥ የጣለው የብልጽግና አገዛዝ መሳሪያ ሆናችሁ ስታገለግሉ ቆይታችኋል፤ በገዛ ህዝባችሁ ላይም መአት አውርዳችኋል” ብሏል ባወጣው መግለጫ፡፡
ይሁንና የአማራ ፋኖ በጎንደር እነዚህ የጸጥታና የታችኛው መዋቅር አካላት የአገዛዙ ታዛዦች ወይም ትእዛዝ ፈጻሚዎች መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ ብሏል፡፡
ይህንንም በመረዳት ዛሬ ከአሁን በፊት ከግንቦት 6 ቀን እስከ ግንቦት 21 ቀን ለ15 ቀናት እንዲቆይ ሆኖ የጸደቀው የምህረት አዋጅ ለተጨማሪ 15 ቀናት፤ ከግንቦት 22 እስከ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲራዘም ወስኗል፡፡
በመሆኑም የአማራ ፋኖ በጎንደርን ለመቀላቀል እና ይሄንን ሰው በላ አገዛዝ ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል መቀላቀል ለሚፈልጉ የጸጥታ አባላት እና የታችኛው መዋቅር አካላት ሙሉ ምህረት ማድረጉን አሳውቋል፡፡
“ወደ አማራ ፋኖ በጎንደር የሚገቡ የጸጥታና የታችኛው መዋቅር አካላት ትጥቃቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው፤ ምንም አይነት ጥያቄ ሳይቀርብባቸው፣ አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷቸው ትግሉን እንደሚቀላቀሉ ሙሉ ማስተማመኛ እንሰጣለን” ሲል አረጋግጧል፡፡
ወደየቤተሰባቸው መሄድ ለሚፈልጉ የጸጥታ አካላት እና የታችኛው መዋቅር አካላት የአማራ ፋኖ በጎንደር ሙሉ ጥበቃ፣ የትራንስፖርት ገንዘብና አልባሳትን የሚያቀርብላቸው ሲሆን በሰላም ወደቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ለማስቻል መዋቅራዊ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ የሚጠቀም መሆኑንም አሳውቋል፡፡
ይህንን የምህረት አዋጅ ያለምንም እንከን ለማከናወንም የአማራ ህዝብ፤ የአማራ ፋኖ በጎንደር የሰጠውን ትእዛዝ በመፈጸም ለምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የጸጥታና የታችኛው መዋቅር አካላት ቀና ትብብር እንዲያደርግና የጸጥታ አካላቱም የምህረት አዋጁን እድል እንዲተቀሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
“የተሰጠው ቀነገደብ ካለቀ በኋላ እድሉን ሳትጠቀሙበት ብትቀሩ ግን ለሚወሰድባችሁ እርምጃ ሀላፊነቱን ራሳችሁ የምትወስዱ ይሆናል” ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
ይህንን የምህረት አዋጅ እንዲያስፈጽሙ ለአማራ ፋኖ በጎንደር ክፍለጦሮችና ብርጌዶች ጥብቅ ትእዛዝ መሰጠቱንም አሳውቋል፡፡አዋጁም የመጨረሻው የምህረት አዋጅ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ላለፉት 15 ቀናት የወጣውን የምህረት አዋጅ በመጠቀም በሽህዎች የሚቆጠሩ የጸጥታ አካላትና የታችኛው መዋቅር አካላት እጃቸውን መስጠታቸውንም ገልጿል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion