የአማራ ፋኖ ወታደራዊ ጉዞ

የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ምርኮኛ የአገዛዙን ወታደሮችን ለገልለተኛ አካላት ይፋ እንደሚያደርግና ማነጋገርም እንደሚቻል አስታወቀ

አንድ ዓመቱን በደፈነው እልህ አስጨራሽ የፋኖ ወታደራዊ ተጋድሎ ከጎንደር ጋይንት ኮረብታዎች እስከ ወሎ ዞብል ተራሮች፤ ከጎጃም ቡሬ ሜዳዎች እስከ ሸዋ መሀል ሜዳ ሰርጦች በርካታ የአገዛዙ ወታደሮች በፋኖ የጥይት ፍላጻ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡

የአገዛዙ መደበኛ ወታደሮች በሞትና በምርኮ ሲያልቁ የሀገር መከላከያ በሚል የዳቦ ስም የሚንቀሳቀሰው ጸረ ኢትዮጵያ ሃይል ተበታትኖ በድሮንና በከባድ መሳሪያዎች ንጹኃንን ከመጨፍጨፍ የዘለለ የአውድ ግንባር ታሪክ ሳይኖረው ቀርቷል፡፡

ባለፉት ወራት ሰራዊታቸው ያለቀባቸው ብርሃኑ ጁላና ተላላኪያቸው አበባው ታደሰ አዳዲስ ምልምሎችን እያስመረቁ ሰሞኑን በገፍ ወደ ጦር ግንባር ልከው የነበረ ቢሆንም ከሽንፈት ማምለጥ አልቻሉም፡፡

ሰሞኑን በአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ የተማረኩ የብልጽግና ወታደሮች በተሰጣቸው የተሃድሶ ስልጠናና ትምህርት ላይ የተገኙት የዕዙ ከፍተኛ አመራሮችም ምርኮኞች በዓለም አቀፍ የጦር ህግ መሰረት ደህንነታቸው ተጠብቆ እንደሚቆዩ ቃል ሲገቡ ተደምጠዋል፡፡

የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ቃል አቀባይ ፋኖ አበበ ሙላቱ ባደረገው ንግግር የአማራ ፋኖ ምርኮኞቹን በተገቢው ሁኔታ እንደሚይዝ ገልጸው አዛዦቻቸው እነብርሃኑ ጁላ ተማረከው በተለቀቁ ሰራዊታቸው ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ድርጊት ምርኮኞችን ለማሰናበት እንቅፋት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በፋኖ ስር የሚገኙ ምርኮኞችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ሀገር በቀል ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በአካል ተገኝተው መመልከትና ማነጋገር እንደሚችሉና ሁኔታው ላይ ምርመራ ማድረግ እንደሚፈቅዱ ይፋ ቃል አቀባዩ ይፋ አድርጓል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በተጨማሪም ገለልተኛ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ዘገባ እንዲሰሩና ምርኮኞችን አነጋግረው እውነታውን እንዲያጋልጡ በራችን ክፍት ነው ሲል ፋኖ አበበ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 


0 Comments

Login to join the discussion