የፋኖ ትግልና ህዝብ አስተዳደር

ራት ኪሎ ላይ ያነጣጠረ የትግል ስልት ቀይሰን እየሰራን ነው ሲል የአማራ ፋኖ በጎጃም ገለጸ

የአማራ ፋኖ በጎጃም መብረቁ ተፈራ ብርጌድ ዋና ጦር አዛዥ ሻለቃ መንበሩ ጌታዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በኦነጋዊ አስተሳሰብ በሚመራው ብልጽግና  አማካኝነት  አማራ ታገተ ተሰቃየ  በግፍ ታሰረ ብሎ ከሰላማዊ ሰልፍ ወደ ተቃውሞ ሰልፍ በመጨረሻም ወደ ትጥቅ ትግል የገባው  የአማራ ፋኖ   ሁሉም ነገራችን  ሕዝባችን  ነው ብሎ ብርጌዳችን  ያምናል ሲል ገልጿል። 

“ሕዝባችን ከሐምሌ 27-2015 ወዲህ የገጠሙትን ችግሮች  እንዲፈቱለት አቤቱታ የሚያቀርበው ወደ ፋኖ ነው።  የመሬት፣ የጋብቻ፦ የልጅ ቀለብ ፣ የወንጀል ጉዳዮች  ወዘተ ሕዝባችን አቤቱታ ወደ እኛ የሚያቀርበው ስለሚያምንብንና የአብራኩ ልጆች ስለሆን ነው” ይላል አዛዡ።

“ከዚህም በላይ በሙሽራው ፋኖ መተዳደር ስለሚፈልግም ነው” ያለው ሻለቃ መንበሩ “የፋኖን ሕዝባዊ ትግል ድል  የሚናፍቁት ሚሊዮኖች ናቸው” ብሏል። 

የሚደግፈንን የሚያምንብንን  ሕዝብ በትሕትና ያለ አድልኦ  ዝቅ ብለን  ማስተዳደር  እንዳለብን ስለምናምን የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው ሲልም ገልጿል፡፡

አማራ ተገደለ ብለን ትግል እንደጀመርን ስለምናውቅ አማራን ላለመጮቆን ብርጌዳችን ከሚያስተዳድራቸው ቀጠናዎች አንድም ግለሰብ ያላግባብ ፍርድ እንዳያጓድል እየጣርን እንገኛለን ሲልም አክሏል። 

አማራ በግፍ ታሰረ ብለን ተቆጭተን  ትግል የጀመርን እኛ የአማራ ፋኖዎች ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ወንጀል ለመፈጸማቸው በሕዝብ ሳይጣራ ወንጀለኛ ብለን መጥራት አቁመናልም ብሏል። 

ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችም  በትክክለኛ ማስረጃና በሕዝብ ምስክርነት ወንጀለኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል ሲልም ስለአስተዳደራቸው ተናግሯል።

የአማራን ሕዝብ በኦሮሚያ ምድር ኦነግ ሸኔ ጨፈጨፈው ፣ ደበደበው፣  ገረፈው  ብለን የትጥቅ ትግል የጀምርን እኛ ፋኖዎች የአማራውን ሕዝብ በተወለደበት ምድር  ካሳደድነው ፣ ከሰደብነው ፣ካንቋሸሽነው  ከሚሊሻና ከፖሊስ የተለየ ግብር እንደሌለን ስለምንረዳ ሕዝባችንን  መብቱን  እናከብራለን ሲልም ገልጿል። 

“ማክበር ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ግዴታ እንዳለብን ፣ ምን ጎደለብህ ብሎ መጠየቅ እንደሚገባን ስለምናውቅ  የመሰረተ ልማት ቅምሻ ማለትም  የጠጠር መንገድ ጥርጊያና የዋጋ ንረትን መከላከል ላይ ትኩረት አድርገን መስራታችንን ብርጌዳችን የሚያስተዳድረው ሕዝባችን ይመሰክራል” ሲል አስታውቋል።  

የአማራን ሕዝብ እኛ መብቱን አክብረን በሌሎች ለማስከበር ወደ ጫካ የወጣንበት ዓላማ ነው ያለው አዛዡ የአማራን ሕዝብ ሌሎች ማክበር ግዴታ ባይጣልባቸውም እንኳ ቀና ብለው እንዳይናገሩት እንዳያሳድዱት ብለን ትግል ጀምረናል ብሏል።

ሻለቃ መንበሩ "እብድ የማይከበረው ራሱን ስለማያከብር  ነው " እንደሚባለው አማራው  የአማራውን ካላከበረ  ሌሎች አማራውን ያከብራሉ  ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ያለም ሲሆን እኛ የሕዝብ ጥቅምና መብት ለማስከበር ወደ ጫካ የወጣን ፋኖዎች ሕዝብን ስናከብር ፣ ስንከባከብ ጫካ ያልወጣው የአማራ ሕዝብ እኛን ያከብራል ይንከባከባል ሲል አስረድቷል።

በተባበረ ክንዳችን ከቀበሌ ፣ወረዳ፣ ዞን ፣ ክልል የነበረውን  የገዥውን ፓርቲ የብልጽግናን መዋቅርና ሰንሰለት ቆራርጠን በታነነዋልም ብሏል።  

“አሁን ብልጽግና ነፍስ ያለው አራት ኪሎ ብቻ ነው ፣  እሱም ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ዓይነት ነው” ያለው ሻለቃ መንበሩ “የአብይ አሕመድ አገዛዝን ለመሸኘት አራት ኪሎ ላይ ያነጣጠረ የትግል ስልት አድርገን እየሰራን ነው” ሲልም አጠቃሏል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion