የብልጽግና ክህደትና የህወሃት ወረራ

የቀጣይ አመት እቅዱን ወልቃይትና ጠለምትን አካቶ ያወጣው ህወሃት ከክረምት በፊት ወደ አካባቢዎቹ እመለሳለሁ ሲል ተሰማ

በህወሃቱ ምክትል ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጌዜያዊ አስተዳደር ግብርና ቢሮ የ2016/2017 የምርት ዘመን እቅድን ሲያወጣ ወልቃይት ፣ ራያና ጠለምትን በእቅዱ ውስጥ ማካተቱ ይታወሳል፡፡

በትናንትናው እለት ደግሞ በራያ እንዳደረገው ሁሉ በአማራ መሬቶች ላይ ወረራ ከመፈጸሙ በፊት በተለያዩ ከተሞች የተፈናቃዮች ሰልፍ አካሂዷል፡፡

ሰልፉ የተፈናቃዮች ነው ቢባልም ህወሃትና የብልጽግናው መንግስት በጋራ ያቀዱትና በጋራ ያስፈጸሙት መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ሰልፍ ላይ በወልቃይትና ጠለምት የታቀደውን በይፋ ያሳወቁት የቀድሞው ቃል አቀባይ ፣ የአሁኑ ፕሬዘዳንት ጌታቸው ረዳ " ከክረምት በፊት ወደ ቄያችሁ እንድትመለሱ ከፌደራልና ከአማራ ክልል መንግስት ጋር እየተነጋገርን ነው " ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ትመለሳላችሁ የሚለውን መልዕክት ለተፈናቃዮቹ ይናገሩ እንጂ በዋናነት የሚያመጡት ታጣቂዎቻቸውን እና አመራሮቻቸውን መሆኑን በራያ የፈጸሙት ተግባር ምስክር ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተባባሪያቸው የብልጽግናው አገዛዝ እና በአረጋ ከበደ የሚመራው የአማራ ብልጽግና ስብስብ መሆኑን አቶ ጌታቸው በንግግራቸው አስረግጠዋል፡፡

ጌታቸው ረዳ አክለውም " የዛሬው ሰልፍ የመጨረሻው እንዲሆንና ከክረምት በፊት እንድትመለሱ ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት እንሰራለን " ብለዋል።

ይህም ወልቃይትና ጠለምትን መውረራቸው አይቀሬ መሆኑን ያመላከቱበት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሃት ታጣቂዎች በዛሬው እለት ወደ ጠለምት ለመግባት 7 ሺህ ወታደር በእንዳባጉና ማስፈራቸውን የጠለምት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ አበበ ተካ ለአንከር ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

ጸሃፊው አክለውም የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳር ዲያቆን ሸጋው ውቤ በጎንደር ከተማ ባደረጉት ስብሰባ “ የህወሃት ታጣቂ ከእነ ሙሉ ትጥቁ ወደ ጠለምት ይግባ” የሚል ትዕዛዝ መስጠታቸውን አንስተዋል፡፡

ነገር ግን አስተዳደሩ እንዳይነካ የሚያደርግ እና ህዝቡን የሚጠብቅ ፋኖ በአካባቢው ተደራጅቷል ይላሉ ጸሃፊው፡፡

በተመሳሳይ ህወሃት ከወር በፊት በወረራ በያዘው በራያ ዓላማጣ የወጣቶች ቁጣ እያየለ መጥቷል። 

የህወሓት ታጣቂዎች በራያ ዓላማጣ ከተማ የሚፈጽሙት ግድያና ዝርፊያ ወጣቶችን ለምሬት ዳርጓል። 

“በብልጽግና ክህደት ተፈጽሞብናል። የዘመናት የማንነት ጥያቄያችን እንደገና ተላልፎ ተሰጥቶብናል” በሚል ወደ አደባባይ የወጡ ወጣቶች የህወሓትን መለያ ሰንደቅዓላማ በማውረድ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ሰቅለዋል።

ከራያ ዓላማጣ ቀበሌዎች በተጨማሪ በራያ ቆቦ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች የህወሓት ታጣቂዎች ወረራ አድርገዋል። 

በዚህም ዋልካ ፣ ሰሌን ፣ ውሃ ኪዳነ ምህረት በመሳሰሉት ቀበሌዎች ታጣቂዎች ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው። እስኪ "የዐማራ ኃይል ይድረስላችሁ" እያሉ ድብደባ ፈጽመውብናል ሲሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

0 Comments

Login to join the discussion