የተጋለጠው የአገዛዙ ቅጥፈት

እነ ሽመልስ አብዲሳ የታገቱ ተማሪዎችን አስለቅቀናል ሲሉ የተለመደ ቅጥፈታቸውን ቀጠሉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች የታገቱ አብዛኞቹ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ቢገልጹም የታጋች ቤተሰቦች ግን ተማሪዎቹ አሁንም ታግተው እንዳሉ ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል ደባርቅ ዩኒቨርሲቲና ከባህርዳር ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሦስት በአውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከ100 የሚበልጡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ይታወሳል።
ከቀናት እገታ በኋላ የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት ባለው እርምጃ 138 ታጋቾች መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጠቅሶ ገልጿል፡፡
18 ተማሪዎች ብቻ አሁንም በእገታ ላይ እንዳሉ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ታጋቾቹ መቼ እንደተለቀቁ ገና እያጣራ መሆኑን አመልክቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የታጋች ቤተሰቦች ግን ዜናው እንግዳ እንደሆነባቸው ገልጸው፤ የታገቱባቸውን ልጆቻቸውን ለማስለቀቅ ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ የታጋች ቤተሰብ “ተማሪዎቹ ሁሉም ተይዞ ነው ያሉት፤ ማንም የተለቀቀ የለም” ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት የሰጡትን መረጃ ሃሰትነት አጋልጠዋል፡፡
በእገታው ስር ካሉ ተማሪዎች መካከል አንድ የቅርብ ቤተሰባቸው እንደሚገኙ የገለጹ አንድ ግለሰብ ትናንት ረቡዕ ጠዋት በአጋቾች ስልክ ተደውሎላቸው ከታገቱት መካከል ማናገራቸውን ጠቅሰው፤ ከ100 በላይ ከሚሆኑ ተማሪዎች ጋር እንደሚገኙ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከእገታው ቀን ጀምሮ ታጋቾችን በቡድን ለይተው እንዲጓዙ ካደረጉ በኋላ ሰኞ ዕለት ወዳልታወቀ አካባቢ ስለመድረሳቸው ገልጸዋል።
“ሁሉም ተሰባስቦ፤ ከ100 በላይ ተማሪዎች አንድ ላይ ነው ያሉት፤ ሁሉም አንድ ላይ ናቸው ተብሎ ተነግሮኛል” ያሉት የታጋች ቤተሰብ፤ “ምንም መፍትሄ እየመጣ አይደለም” ሲሉ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣታቸውን ተናግረዋል።
“ከታጣቂዎች ጋር ሰላም ፈጥረን፤ ብር ከፍለን የሚሰጡን ከሆነ ማስወጣት ነው። መንግሥት ምንም ነገር እያደረገ ስላልሆነ የመንግሥትን ነገር ትተናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እኚሁ ወላጅ ለመንግሥት ስለታገቱት ተማሪዎች መረጃ ማድረሳቸውን የገለጹም ሲሆን፤ የተጠየቀውን ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍሎ ከማስለቀቅ ውጪ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም ብለዋል።
“ብዙ መረጃ ተሰብስቧል፤ ብዙ ነገር ተጠይቀን አናግረናል፤ አልቅሰናል፤ ጮኸናል። ለልጆቹ መብት የደረሰ ማንም የለም። ስለዚህ እኛ ብር ከየትም ከየትም ብለን የምናገኝ ከሆነ፤ ከእነሱ ጋር አልቅሰንም ይሁን ለምነናቸው ልጆቻችንን ማስመለስ ነው የምንፈልገው። ምንም መፍትሄ ስለሌለ ተስፋ ቆርጠናል” ብለዋል።
“ቤተሰቦቻችሁ ላይ ደውሉና ብር ያስገቡ እያሉ እያስፈራሯቸው ነው፤ እስካሁን ድረስ እዚያ ነው ያሉት” ያሉት ሌላ ወላጅ፤ የልጃቸው ሕይወት አደጋ ላይ እንዳለ ተናግረዋል።
“ታጣቂዎች ‘ዛሬ የመጨረሻ ቀን ነው፤ ብዙ ደክማችሁ በኋላ ትሞታላችሁ’ እያሏቸው ነው። በፊት ደረቅ ዳቦ ይሰጡ ነበር፤ አሁን እሱን ራሱ አንሰጣችሁም እያሉ ነው። አንድ ነገር ያደርጉናል” ብለውናል የሚሉት ወላጅ ፣” እኛ ራሱ በስጋት ላይ ስላስቀመጡን፤ ገበያ ውስጥ ጨርቅ ዘርግተን እየለመንን ነው” ተናግረዋል፡፡የታጋች ቤተሰቦች ይህን ቢሉም ቅጥፈት የማይሰለቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ግን “የፀጥታ ኃይሎች” በወሰዱት እርምጃ 160 ተማሪዎች ተለቀዋል ብሏል።
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ከታገቱት 167 ተማሪዎች ውስጥ ሰባት ተማሪዎች ብቻ አለመለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የብልጽግናው መንግስት ከዚህ ቀደምም 17 ተማሪዎች በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲታገቱ አስለቅቄያለሁ የሚል የሃሰት መረጃ አሰራጭቶ ህዝቡን ማደናገሩ ይታወሳል፡፡
አሁንም ለህዝቡና ለዜጋው ካለው ንቀት የተነሳ በዚህ ጉዳይ ላይ ከማደናገር የዘለለ መፍትሄ እንደሌለው ይታወቃል፡፡
ሆኖም የታጋች ቤተሰቦች ልጆቻችን አልተለቀቁም በሚሉበት ወቅት በደሃ ልጅ የሚቀልደው አገዛዝ አስለቅቄያለሁ በሚል የሚዲያውንና የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመንፈግ እየጣረ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከሳምንታት በፊት የአቶ ሽመልስ አብዲሳ እናት ታግተው በ10 ሚሊዮን ብር ለማስለቀቅ 3 ሰዓታት ብቻ ነበር የወሰደበት፡፡

0 Comments

Login to join the discussion