የአላማጣው ሰልፍ

ወደ አላማጣ ከተማ የታጣቂ ኃይሎች እየገቡ በመሆናቸው ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄደ ነው
ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ አላማጣ ከተማ እየተመለሱ ካሉ ተፈናቃዮች ጋር “ታጣቂ ኃይሎች አብረው እየገቡ በመሆኑ” ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በከተማይቱ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል። ህወሃት ግን በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን የሚገልጹትን ሰዎች የፕሪቶሪያው ስምምነት “ውድቅ እንዲሆን የሚፈልጉ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ናቸው” ሲል ነው የተሰማው፡፡
ህወሃት ከ19 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ናቸው ያላቸውንና ታጣቂዎችን እያስገባ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡ከእነዚህ ተፈናቃዮች ጋር የህወሃት ታጣቂ ኃይሎች አብረው እንዲገቡ በመደረጉም  የአላማጣ ነዋሪዎች  ተቃውሟቸውን ለማሰማት ትናንት እና ከትላንት በስቲያ አደባባይ መውጣታቸውን የአይን እማኞች አስታውቀዋል።
በቦታው የነበሩ አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ የትላንትናው የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው “ወንጭፍ አደባባይ” በሚባለው ቦታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ ወደ አላማጣ የገቡት በአውቶብስ፣ በሚኒባስ እና በሞተር ሳይክል ተጭነው እንደነበር የጠቀሱት እኚሁ ነዋሪ፤ እነርሱን ያጀቡ አራት አምቡላንስ መመልከታቸውን ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የትግራይ ክልል ባንዲራን ይዘው እንደነበርም ተናግረዋል።
“እንዲህ ሆነው ሲገቡ ወጣቱ አትገቡም አለ። ወዲያው መከላከያ መጥቶ ነገሩን እንዲረጋጋ አደረገ። እነሱም ወደ ስታዲዮም እንዲሄዱ ተደረገ” ሲሉ ትላንት የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል። በትላንቱ ሰልፍ “ህዝቡ በሰላም ነው ተቃውሞውን ያሰማው” ያሉት ነዋሪው፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የተቃውሞ ሰልፍ በወጣቶች መደረጉን ገልጸዋል።
ወደ አላማጣ ከተማ እየተመለሱ ያሉት ተፈናቃዮች “በትክክል የከተማው ነዋሪዎች አይደሉም” የሚሉት ነዋሪው፤ ለተቃውሞው መቀስቀስ ምክንያት የሆነውን ጉዳይም ይኸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ለሁለት ቀናት ወደ አላማጣ ከተማ እንዲገቡ ከተደረጉት ተፈናቃዮች ውስጥ የተወሰኑት፤ “ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ ተመልሰው መጥተው አብረውን ሲኖሩ የነበሩ ናቸው” ሲሉም ይሟገታሉ።
“በዚህ ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት፤ የትግራይ ክልል መንግስት አላማጣ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የክልሉን ተወላጆች የገንዘብ እና የተለያዩ ድጋፎችን ታገኛላችሁ በሚል ወደ መኾኒ ከተማ እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል። ትላንት ወደ አላማጣ እንዲገቡ የተደረጉት ተፈናቃዮች እነዚሁ ወደ መኾኒ የተወሰዱት እና ታጣቂዎች ተቀላቅለው ነው” ሲሉም ነዋሪው ይከስሳሉ።
ከተፈናቃዮቹ ጋር “መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችን” መመልከታቸውንም ለዚህ በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። “እኔ በአይኔ ያየሁት፤ አምስት እና ስድስት ሞተር ላይ [የተሳፈሩ] ክላሽ የያዙ ናቸው። ክላሹ ጥቁር ታጣፊ፣ መከላከያ የሚይዘው ዓይነት ነው። ‘ተፈናቃይ ነኝ’ እያልክ እንዴት መሳሪያ ትይዛለህ?” ሲሉም ነዋሪው ይጠይቃሉ።
እርሳቸውን ጨምሮ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች፤ “ትክክለኛ” ሲሉ የሚገልጿቸው ተፈናቃዮች ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን በመጥቀስ ይከራከራሉ።
ሶስቱም ነዋሪዎች አሁን እየተደረገ ያለው “ተፈናቃዮችን ሳይሆን ታጣቂዎችን ወደ ከተማይቱ የማስገባት ስራ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion