የአማራ ክልሉ ውጊያና የጀነራሉ መልዕክት

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰማ

የብልጽግናው አገዛዝ “ፋኖ እየተበተነ ነው” በሚልበት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፋኖዎች ተዋጊዎችን እያሰለጠኑ ፣ እያደራጁ እና የብልጽግናን ጦር በከባድ ውጊያ መውጪያ መጊያ እያሳጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአማራ ፋኖ በጎንደር እዝ በዛሬው እለት በምዕራብ ጎንደር ቋራ አካባቢ ካራ ማራ በሚል ስያሜ ክፍለጦር ማቋቋሙ ተሰምቷል፡፡ ይህም በጎንደር ምድር 22ኛው ክፍለጦር መሆኑ ተነግሯል፡፡
በምዕራብ ጎንደር መተማም በዛሬው እለት የአካባቢው የብልጽግና ባለስልጣን በፋኖዎች ተይዞ መወሰዱ ተሰምቷል፡፡ የፋኖ ሃይሎች ማንነቱን በይፋ ያልገለጹት የብልጽግና ባለስልጣን በፋኖ መወሰዱን ተከትሎ የአገዛዙ ጦር ድንብርብር ውስጥ መግባቱ ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል በምስራቅ ጎጃም ከደብረማርቆስ ወደ ደብረ ኤሊያስ ሲጓጓዙ በነበሩ የአገዛዙ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ የፋኖ ሃይሎች ቀረር በተባለ ቦታ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ በጎጃም ምዕራባዊ ክፍል ቋሪት ወረዳ ጠጠር ማርያም በተባለ አካባቢ ከማለዳው ጀምሮ እስከ 4 ሰዓት ድረስ የዘለቀ ውጊያ ተካሂዷል፡፡
ውጊያው የቆመውም የብልጽግና ጦር አካባቢውን ለቆ በመውጣቱ ነው፡፡
ከሞጣ አዴት በሚወስደው አቅጣጫ አስትሮይ እና አንበሲት በተባሉ አካባቢዎች የደፈጣና የፊት ለፊት ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ በዚህም በአገዛዙ ጦር ላይ ከባድ ኪሳራ ተስተናግዷል፡፡
በደጋ ዳሞትም በተመሳሳይ ረፋዱን ጀምሮ በሶስት ቦታዎች ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡
በተለይም የብርሃኑ ጁላ ጦር አባላት ጉድባ ሰቀላ የተባለውን ቦታ ለመያዝ ባደረጉት እንቅስቃሴ ጀፈር ፣ ሚካኤልና ዝቋላ ካምፕ በተባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ ውሏል፡፡
በዚህም ፋኖዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን የአገዛዙን ጦር አባላት መያዛቸውና ቀላል የማይባሉትን ሙትና ቁስለኛ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
በደንበጫ ፣ በዳንግላ እና በሌሎች የጎጃም አካባቢዎች ውጊያና ተኩሶች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎችም የአገዛዙ ጦር አባላት በፋኖ የሚደርስባቸውን ሽንፈት ተከትሎ ንጹሃንን እየጨፈጨፉ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አገዛዙ በግሽ ዓባይ የከፈተው ጥቃትና የሞከረው አፈና ከሽፎበት መሸሹንም ለማወቅ ችለናል፡፡
የአማራ ፋኖ የጎጃም አገው ክፍለ ጦር ሰራዊት የጊዮን ብርጌድ ሰብሳቢ ፋኖ መምህር ተፈራ ለኤቢሲ በሰጠው ቃል በግሽ አባይ ፋግታ መስመር ከበባ አድርጎ የነበረው ጠላት ጠላት መሸሹንም አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ “ከአርበኛ አሰግድ መያዝ ጋር ተያይዞ ብዙ የድምፅ ቅጅዎች በስልኩ እንደተገኙ አድርጎ አገዛዙ በራሱ ሚዲያዎች ሊያራግብ እንደሆነ መረጃው ቀድሞ ደርሶናል” ሲሉ ፋኖን የተቀላቀሉት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ተናግረዋል፡፡
“ስለሆነም ትግሉን ለማጠላለፍ የአማራን ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ በተለይም መሪዎችን ሊያጓትት የሚችል ሴራ እየሰራ መሆኑን ተደርሶበታል” ብለዋል።
“በዚህም ምክንያት መላው የአማራ ህዝብ ከወዲሁ ነቅቶ ትኩረቱን ትግሉ ላይ ብቻ እንዲያደርግ ለሚቀርቡ ማንኛውም ዶክመንተሪ የድምፅ ቅጅ የመሪዎቹ እንዳልሆነና በአርቴፍሻል ኢንተለጄንስ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ መሆኑን እንዲያውቅ እናሳስባለን” ሲሉ ጀነራሉ መግለጻቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡

0 Comments

Login to join the discussion