አይቀሬው የውጭ ምንዛሬው ጭማሪ

የብልጽግናው አገዛዝ በቅርቡ የዶላር ምናዛሬን ከ15 እስከ 20 በመቶ ለመጨመር መወሰኑ ተሰማ

የኢትዮጵያ የብር  የውጭ ምንዛሬ ተመን የመዳከሙ ወይንም ሌላ አማራጭ እርምጃ የመወሰዱ ነገር በእጅጉ መቃረቡን ከምንጮቼ ሰምቻለሁ ስትል ዋዜማ ዘግባለች፡፡
በተለይ ከሰሞኑ በዶላር የሚከፈላቸው የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሰራተኞች በእጃቸው ያለ የውጭ ምንዛሬን ወደ ባንክ ለመመለስ ሩጫ ላይ መሆናቸውም በዘገባው ተነስቷል፡፡
ይህም የሆነው መንግስት የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመንን የሚያተካክል ከሆነ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎችን ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቦርድ የፊታችን ሰኞ ለኢትዮጵያ በሚሰጥ ብድር ላይ ይወያያል መባሉም ግምቶችን አጠናክሯል።
ለወትሮ አይኤም ኤፍ ለሀገራት ብድርን በቦርድ ከማጽደቁ በፊት በታችኛው አደረጃጀት ጉዳዩን ይፋ አድርጎ ነው ወደ ቦርድ ማጽደቅ የሚሄደው።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ለሰኞ የተቀጠረው የአይኤምኤፍ የቦርድ ስብሰባ ግን ከቅደም ተከተል አንጻር ያልተለመደ ነው።
አቢይ ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከእነዚህ ተቋማት ጋር ስምምነቱ ሲያልቅ 10 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ኢትዮጵያ ታገኛለች ማለታቸው ይታወሳል።
ስለ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ኢትዮጵያ ድርድሩን በስምምነት ብትቋጭ ራሱ ግፋ ቢል ከስድስት እስከ ሰባት ቢሊየን ዶላር ብታገኝ ነው ይላሉ።
የዐቢይ አገዛዝ የታክስ ፤ የባንክ ስራ አዋጅን ፤ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ገንዘብ የሚያገኝባቸው ሁኔታዎች እንዲገደቡ እንዲሁም ብሄራዊ ባንክን በወለድ ተመን ምጣኔ የሚመራ ባንክ ማድረግን ጨምሮ በአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚቀርቡ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቷል ፤ እያሟላም ነው። አሁን ላይም ቀረ የሚባል ነገር ቢኖር የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ጉዳይ ብቻ ነው።
እንደዋዜማ ዘገባ ከሆነ የዐቢይ አገዛዝ ብድሩን ለማግኘት  በሚዳከምበት ምጣኔ ላይ እንጂ በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከም ላይ ከስምምነት ከደረሰ ሰንበትበት ብሏል።
መጀመርያ ላይ የእነ አይ ኤም ኤፍ ፍላጎት የኢትዮጵያ ብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ነበር። ይህን የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት የሚተገብረው እንዳልሆነ በግልጽ ማስቀመጡ ይታወሳል። ቀጥሎም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን እስከ 90 በመቶ እንዲዳከም የአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ፍላጎት ነበር ። አሁን ላይ ግን ከበርካታ ድርድሮች በኋላ  የኢትዮጵያ መንግስት የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን ከ15 እስከ 20 በመቶ ሊያዳክም ፤ በተጨማሪም በየጥቂት ጊዜው ብርን ለማዳከም መስማማቱንም ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ይህም እጅግ በጥቂት ጊዜ የሚፈጸም መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን መዳከሙ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ዋና ዋና ምርቶችን ከውጭ ገዝቶ ለሚያስገባ ሀገር ከባድ የዋጋ ንረትን ማምጣቱ አይቀሬ ነው።
የረከሰ ገንዘብ እንደ ቻይና ላሉ አምራች ሀገራት ጥሩ የሆነ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን አስገኝቷል።እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ነዳጅን በአራት ቢሊየን ዶላር አስገብተው ቡናን በአንድ ቢሊየን ዶላር ለሚሸጡ ሀገራት ግን የመገበያያቸውን ገንዘብ የምንዛሬ ተመን ማዳከም ውጤቱ ወደ ዋጋ ንረት እንደሚያደላ ያለፉት ጥቂት አመታትም ምስክር ናቸው።

0 Comments

Login to join the discussion