ዐቃቤ ህጉ የተዋረደበት የችሎት ውሎ

ትናንት በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት የቀረቡ የህሊና እስረኞች “ነጻ የሚያወጣን የዳኛ ውሳኔ ሳይሆን ፣ ፋኖ ነው” ሲሉ ተደመጡ

በእነ ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የተከሰሱ የህሊና እስረኞች በትናንትናው እለት ፍርድ ቤት ቀርበው የአገዛዙን ማንነት የሚገልጽ ንግግር በድፍረት ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የህሊና እስረኞቹ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሲገርፋቸው የነበረውን ግለሰብ በፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ሆኖ በማግኘታቸው ግርግር ተፈጥሯል፡፡
በትናንትናው እለት በብልጽግናው አገዛዝ ፍላጎት በሚመራው ፍርድ ቤት ከቀረቡትና አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው አንዱ ነው።
ጋዜጠኛ ዳዊት በችሎቱ ያሰማው ባደረገው ንግግር ዳኞቹ ለአለቆቻቸው ታዛዥነት እንጂ ሙያዊ ክብርም ሆነ ህሊናቸውን የሚያዳምጡ እንዳልሆኑ ገልጿል።
"የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሀገሪቱ ህገ መንግስት ውጭ ለ 3ኛ ጊዜ ለመመረጥ ፈለጉ። የኬንያ ፍርድ ቤት ግን አትችልም ብሎ አሰናበታቸው። የኬንያ ህዝብም ዊሊያም ሩቶን መምረጥ ቻለ። እናንተ ዐቢይ አህመድ እንደዛ ቢላችሁ እምቢ ትሉታላችሁ?” ሲል ጠይቋል ዳዊት፡፡
ዳዊት አክሎም “የሴኔጋል ፕሬዝዳንት የነበረው ማኪ ሳል ምርጫ የማደርገው በሚቀጥለው ታህሳስ ነው ቢልም የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ግን በ 20 ቀን ውስጥ ምርጫ አድርግ ብሎ አዞት አደረገ። እናንተ እንደ ሴኔጋል ዳኞች ትሆናላችሁ" ብሏል።
በመጨረሻም "ለማንኛውም እናንተም አስር መዝገብ  ከምትከፍቱ ተከሳሽ ሁሉም የአማራ ህዝብ በሉት" ሲል የፍርድ ቤቱን ወገንተኝነት በግልጽ ተናግሯል።
በተመሳሳይ መንበር አለሙ “እናንተን መናገር አንፈልግም፤ ነገር ግን የአገዛዙ ፍርፋሪ ለቃሚ አትሁኑ። አቃቤ ህግ መቸም የአገዛዙ ፍርፋሪ ለቃሚ ነው። ከዚህ አካል ምንም አንጠብቅም። ክንዳችን ነጻ ያወጣናል ፤ ክንዳችን ደግሞ ፋኖ ነው።” ብሏል ለችሎቱ።
በሌላ በኩል የአማራን ሕዝብ ከየአቅጣጫው እየሰበሰበ ወደ ማጎሪያ የሚያወርደው የብልጽግና አገዛዝ ከ10 በላይ የሚሆኑ የሽብር ክስ መዝገቦችን አዘጋጅቶ የአማራ ተወላጆችን ከሷል።
ከእነዚህ የክስ መዝገቦች ውሰጥ የነዶክተር ወንዶሰን አሰፋ፣ የነዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም፣ የነስንታየሁ ንጋቱ እና ሌሎች መዝገቦችም ለ25/11/2016 ዓ.ም ተቀጥረው በአንድ አዳራሽ ቀርበው ነበር።
ታዲያ በእነዚህ መዝገቦች ላይ የፍትሕ ሚኒስትርን የሀሰት ክስ ለማስረዳት ከቀረቡ ዓቃቢያን ሕግ መካከል ሙላቱ ሺበሺ የሚባለው ይገኝበታል።
ሆኖም ሙላቱ ሺበሺ ዓቃቤ ሕግን ወክሎ በፍርድ ቤቱ ሲገኝ ያላሰበው ዱብዳ ገጠመው።
በፍርድ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ጢም ካለው ቢጫ ለባሽ የአማራ ተከሳሽ መካከል በፌዴራል ፖሊስ ማጎሪያ ውስጥ ዘቅዝቆ ቶርች ያደረጋቸው እና ክፉኛ ከተጎዱት አማሮች ጋር ተፋጠጠ።
ይህ ባለብዙ መልክ የሥርዓቱ ሰው ከፌዴራል ፖሊስ የፀረሽብር ወንጀል መከላከል ኃላፊ ከሆነው ኮማንደር አዱኛ ረጋሣ ጋር በመሆን በነዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም መዝገብ የተከሰሱትን ብርሃኑ ስለሺንና ሕይወት ዓለማየሁን በእግር ብረት አስሮ በመዘቅዘቅ በኤሌክትሪክ ሽቦ መግረፉን የግፍ ሰለባዎቹ በከፍተኛ ቁጣ ለዳኞቹ አስረድተዋል። እንዲሁም በነስንታየሁ ንጋቱ መዝገብ የተከሰሱትም ዓቃቤ ሕግ ተብሎ በፍርድ ቤት የተሰየመው ሙላቱ ሺበሺ ልብሳቸውን አስወልቆ እንደገረፋቸው ለችሎቱ አስረድተዋል።
ሌሊት ሌሊት አማሮችን ቶርች የሚያደርገው ሙላቱ ሺበሺ ቀን ቀን የበግ ለምድ በመልበስ ፍትሕ ለማዛባት እና ለማጓተት ችሎት በመገኘቱ በሥርዓቱ እጅግ ማዘናቸውን ሰለባዎቹ ገልጸዋል።
ሌሊት ፖሊስ፣ ገራፊና ዘራፊ ፥ ቀን ቀን ደግሞ ካባቸውን ቀይረው  ዓቃቤ ሕግ እና ዳኛ በሆኑ የሥርዓቱ ተላላኪዎች ፍትሕ እናገኛለን ብለን አናምንም በማለትም የሥርዓቱን ዝቅጠት አጋልጠዋል።
በተፈጠረው ክስተት የተደናገጠው ዓቃቢ ሕግ ሙላቱ ሽበሽ መዝገባቸው ለዛሬ አልተቀጠረም ለምን ዛሬ መጡ በማለት በዳኞች ላይ የቁጣ እና የግልምጫ ናዳ ያወረደባቸው ሲሆን ዳኞችም በመደናገጥ ፍርድ ቤቱ የቀጠራቸው የሰበዓዊ ጥሰትን በተመለከተ የቀረቡ አቤቱታዎችን ለመስማት መሆኑን ገልጾ ገራፊ እና ዘራፊውን ዓቃቢ ሕግን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ገራፊና ዘራፊን ሃይል ይቅርታ እየጠየቀ ተበዳይ ላይ የሚፈርድ መሆኑን አሳይቷል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion