የፋኖዎቹ የጋራ መግለጫ

“አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በመደገፍ ታሪካዊ ስህተት እየሰሩ ነው” ሲል ፋኖ ገለጸ

የአማራ ፋኖ በጎንደር ፣ የአማራ ፋኖ በሸዋ እዝ ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃምና የአማራ ፋኖ በወሎ በጋራ በመሆን ለአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /IMF/ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጄቫ እና ለአለም ባንክ ዋና ዳይሬክተር አጃዬ ባንጋ በኢትዮጵያ ላይ የወሰኑትን ውሳኔ እንዲያጤኑት የሚጠይቅ መግለጫ አውጥተዋል፡
ሁለቱ የገንዘብ ተቋማት በአብይ አህመድ ለሚመራው የብልጽግና አገዛዝ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ድጋፍ በማጽደቃቸው ቅሬታ እንደገባቸው ነው የፋኖ እዞቹ በመግለጫቸው ያሰፈሩት፡፡
የገንዘብ ድጋፉ የተፈቀደው የአብይ አገዛዝ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጭምር በመጣስና የአገሪቱን ሃብት በመጠቀም የራሱን ዜጎች ጦርነት ከፍቶ በንቃት እየጨፈጨፈ ባለበት ወቅት በመሆኑ የተፈቀደው ብድርና ድጋፍ አግባብ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
ከአለም አቀፍ አጋሮች የተገኘውን ድጋፍ በውድቀት ላይ ያለው የአብይ አስተዳደር የአማራን ህዝብ ለመጨፍጨፍ እንደሚጠቀምበትም ተቋማቱ ሊያምኑ ይገባል ሲሉ የፋኖዎቹ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ላለፉት 15 ወራት የአብይ አህመድ ወታደሮች በአማራ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች ንጹሃን ሰዎችን ፣ ሴቶችን ፣ ህጻናትን እና አረጋውያንን በግፍ መግደላቸውን አለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸውንም ለአብነት አንስቷል መግለጫው፡፡
መግለጫው አክሎም በእነዚህ ጊዜያትም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዋጋ እየከፈሉ ሲሆን ፣ በከባድ መሳሪያ ፣ በድሮን ጭፍጨፋ ፣ በጾታዊ ጥቃት ፣ በማንነት ተኮር ጅምላ እርስ እንዲሁም ድብደባና ግርፊያ ህዝባችን እየተሰቃየ ነው ብሏል፡፡
ተቋማቱ በብድርና በድጋፍ ያጸደቁት ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ጠቀሜታም ሆነ እፎይታ እንደማይሰጥም የፋኖ ሃይሎቹ ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ህዝብ ደግሞ ላለፈው አንድ አመት የዘር ማጥፋት ጦርነት ታውጆበት ከሰብዓዊ ድጋፍና ከግንኙነት ውጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ አብይ አህመድና ካቢኒያቸው ደግሞ 20 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ በሚፈልግበት ወቅት በ10 ቢሊዮን ዶላሮች ቅንጡ ቤተመንግስት እያሰሩና የሃገር ሃብት እያባከኑ መሆናቸውንም እነ ምሬና እነ ዘመነ በጥምረት ያወጡት መግለጫ ያመለክታል፡፡
በደብዳቤው በነጮቹ 1994 እነዚሁ አለም አቀፍ ተቋማት ለሩዋንዳ መንግስት ድጋፍ ካደረጉ በኋላ በአገሪቱ የተነሳውን የርስ በርስ እልቂት በማስታወስ አሁንም ለአብይ አህመድ አገዛዝ እንዲህ አይነት ድጋፍና ብድር ማድረግ የርስ በርስ እልቂትን እንደሚያዋልድና የአገር ሃብትን በሙስኞች ከማዘረፍ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡
የሩዋንዳውን ስህተት እነ አይ ኤም ኤፍ እየደገሙት መሆኑን ያነሱት ፋኖዎቹ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ፍትህና ተጠያቂነትን ከግምት ውስጥ እንዳላስገቡም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአማራ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በመደገፍ ታሪካዊ ስህተት እየሰሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋል ፋኖዎቹ፡፡
በአጠቃላይ የፋኖ እዞቹ በጋራ በጻፉት መግለጫ የአለም አቀፍ ተቋማቱ ይህን ስህተት የሆነ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ከመተግበሩ በፊት ዳግም ሊያጤኑበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሆነው ሆኖ የህዝባቸውን መብት ፣ ክብርና ነጻነት ለማረጋገጥ የአብይ አህመድን ስርዓት ለመጣል እንደሚታገሉም ፋኖዎቹ ገልጸዋል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion