በደቡብ ጎንደር የፈረሰው የብልጽግና ሃይል

በደቡብ ጎንደር አካባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች ፋኖ አንድ የአገዛዙን ዋነኛ ክፍለጦር ማፈራረሱ ተገለጸ

ምሽግ ደርማሹ በሚል ቅፅል ስም የሚጠራውና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው 92ኛ ክ/ጦር በጎንደር አናብስቶች ከባድ ኪሳራን አስተናግዶ ወደ ኋላ መሸሹ ተሰምቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 27/2016 ዓ/ም ከንጋት ጀምሮ በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንትና ታች ጋይንት እንዲሁም በትናንትናው እለት ደግሞ በደብረታቦር፣ በወረታ፣ በሐሙሲት ፣ በአዲስ ዘመንና በክምር ድንጋይ በተደረገ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ 92ኛ ክ/ጦር ወታደሮች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን የአማራ ድምፅ ውጊያውን የመሩ የፋኖ አዛዦችን አነጋግሬ አረጋግጫለሁ ሲል ዘግቧል፡፡
92ኛ ክ/ጦር በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ስር ከሚገኙ ክ/ጦሮች መካከል አንዱ ሲሆን ይህ ክ/ጦር የዕዙ የጀርባ አጥንት እና ምሽግ ደርማሽ በመባል ይታወቅ ነበር ተብሏል።
ክ/ጦሩ ከትናንት በስቲያ ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ትናንት ሙሉ ቀን ከወደ ጎንደር ፋኖዎች በተሰነዘረበት ከባድ ምት በርካታ ወታደሮቹ ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ፡ ቀሪዎቹ ሕይወታቸውን ለማትረፍ እግር ወዳመራቸው እየሸሹ መሆኑንም ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡
ከትናንት በስቲያ ሃምሌ 27/2016 ዓ/ም ከንጋት ጀምሮ የደቡብ ጎንደር ዞን መናገሻ በሆነችው በታሪካዊቷ ደብረታቦር ከተማ ልዩ ስማቸው ግራር ሰፈር፣ መሎ፣ ጎንደር በርና አባረጋይ በተባሉ የከተማዋ ሰፈሮች ላይ ከባድ ውጊያ የተደረገ ሲሆን በዚህም የጠላት ብልፅግና ፓርቲ አገልጋይ የሆኑት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ወታደሮች ከባድ ኪሳራን አስተናግደው ከተማዋን ለቀው መሸሻቸው ተሰምቷል።
ወደ ከተማዋ ዘልቀው የገቡት በአማራ ፋኖ በጎንደር የጉና ክ/ጦር እና የጄነራል ነጋ ተገኝ ክ/ጦር ሁለት ብርጌድ ፋኖዎች፡ አገዛዙ "ፋኖ የሆነ ቤተሰብ አላችሁ ወይንም ለብልፅግና ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍ አላደረገም ብላችኋል" በሚል ምክኒያት በርካታ ንፁኋንን አስሮ ሲያሰቃይበት የነበረውን 1ኛ ፖሊስ ጣቢያን በእሳት እንዳቃጠሉትም ነው የከተማዋ ነዋሪዎች የገለፁት።

የፋኖ አባላቱ በከተማዋ አስፈላጊ ስራዎችን ከሰሩ በኋላ ኢኒስፔክተር ያለው የተባለ የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ የፀጥታ አመራርን ከነ አጃቢዎቹ በመያዝ የማረኩትን መሣሪያ አሸክመው ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውም ታውቋል።
በተመሣሣይ በጄነራል ነጋ ተገኝ ክ/ጦር የአሳምነው ፅጌ ብርጌድ ፋኖዎች ወረታ ከተማን ለግማሽ ሰዓታት ያህል በቁጥጥራቸው አድርገው የዋሉ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ ተቆርጠው የአብይ አህመድ ወታደሮችንና ሆድ አደር የአድማ ብተና እንዲሁም የሚሊሻ አባላትን ካፀዱ በኋላ ከተማዋን ለቀው መውጣታቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በዚኸው በጄነራል ነጋ ተገኝ ክ/ጦር ስር የጣና ገላውዲዎስ ብርጌድ ፋኖዎች የደራዋ ሐሙሲት ከተማን በቁጥጥራቸው ስር ሲያደርጉ በተመሣሣይ ሰዓት አዲስ ዘመን ከተማ በጣይቱ ክ/ጦር ፋኖዎች መዳፍ ስር መግባቷ ነው የተዘገበው፡፡
የጋፋት ክ/ጦር ፋኖም እንዲሁ ክምር ድንጋይን እና ሌሎች በዙሪያው ያሉ አከባቢዎችን መቆጣጠሩ ነው የተሰማው።
ከትናንት በስቲያ በፋኖ ቁጥጥር ስር የገቡትና የገዢው ቡድን ጦር ከባድ ኪሳራን ያስተናገደባቸው የላይ ጋይንትና የታች ጋይንት አከባቢዎች ዛሬም በሚወዷቸውና በሚሳሱላቸው የቁርጥ ቀን ልጆቻቸው መዳፍ ስር መሆናቸው ታውቋል።
የአማራ ፋኖ በጎንደር በሻለቃ ከፊያለው ደሴ የሚመራው የገብርየ ክ/ጦርና የአማራ ፋኖ በወሎ መቅደላ ፅናት ክ/ጦር ስር የሚገኙ ሁለት ሻለቃ ፋኖዎች በቅንጅት በፈፀሙት ኦፕሬሽን ላይ ጋይንትንና ታች ጋይንትን በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸውንም ሮሃ መዘገቧ አይዘነጋም፡፡

0 Comments

Login to join the discussion