የእነ ኮለኔል ደመቀ ውሳኔ

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን “መከላከያ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሰርጎ ገቦችን ለመታገል ተነስቻለሁ” ሲል አስታወቀ

 በአቶ አሸተ ደምለው ዋና አስተዳዳሪነትና በኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ምክትል አስተዳዳሪነት የሚመራው ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

አስተዳደሩ በመግለጫውም ወልቃይት-ጠገዴ በመላ አማራ ትግል  ነጻ ወጥቷል ያለ ሲሆን፣ “ሕዝባችንም የተነጠቀ ማንነቱን ዳግም በግፈኞች እንዳይነጠቅ ከምን ጊዜውም በላይ ራሱን አደራጅቶ እየጠበቀ ይገኛል” ሲል ገልጿል፡፡፡፡ 

“ሆኖም ግን የጥፋት መንገዱ ብዙ የሆነው ህወሃት ዞኑን መልሶ ለመያዝ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሙከራዎችን አድርጓል” የሚሉት እነ ኮለኔል ደመቀ፤  “ጥቃቱ የተልዕኮና ቀጥታ፤ የተቀናጀና የዕቅድ ደረጃዎች  ያሉት ሆኖ ታይቷል” ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ 

በወታደራዊና በደህንነት ሙከራዎች ያልተሳካለት ህወሃት የማንነት ኮሚቴዎችን ስም በማጠልሸት ከህዝብ ለመነጠል ሙከራ አድርጓል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለፖለቲካ ዓላማ በልዩ ሁኔታ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ ገዳይ ቡድን ከትግራይ መልምሎ ወደዞኑ በማስገባት ኮር አመራሩን የማጥቃት ሙከራዎችን አድርጓል በማለትም አንስቷል መግለጫው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች መክሸፋቸውን ገልጿል፡፡

ህወሃት በቀጣይም ሰርጎ ገቦችን አስገብቶ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት አቅዷል የሚለው የወልቃይት አስተዳደር ፣ “አስተዳደሩ ጠላቱን የሚከላከልበትን ለአከባቢው ነዋሪዎች ያስታጠቀውን የጦር መሣሪያ ማስፈታት፤ የማንነትና የወሰን አስተዳደር መዋቅርን ማፍረስና ፀረ-ማንነት ትግል ሆኖ መታየት ፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የተደራጀውን የማንነት አደረጃጀት ዶክመንቶችን፣ ፋይሎችንና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ማቃጠልና ማውደም” ሲልም አስትውቋል፡፡ 

በአውራ ወረዳ ሎሚ ወንዝ ቀበሌ ፣ ጠገዴ ወረዳ አዳይጦ እና በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በእድሪስ ቀበሌዎች ባሉ አካባቢዎች ላይ በመከላከያ ላይ ትንኮሳ ተፈጽሟል ብሏል፡፡

ትንኮሳውን የፈጸሙትም ከህወሃት ውክልና የወሰዱ ሃይሎች መሆናቸውን አረጋግጠናል ሲል ገልጿል፡፡

መግለጫው “ችግራችን ውስብስብ፣ የሁሉንም ወገን አገራዊ ትብብር የሚጠይቅ፣ ጊዜ የማይሰጥ፤ ምንም ዓይነት ስህተት ሊታይበት የማይገባ በመሆኑ፤ የወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የትርምስ ቀጠና እንዳይሆን የፋኖ ኃይሎች ወደ ዞኑ ከመግባት ተቆጥበው ያሉ መሆኑ እየታወቀ፤ የወቅቱን የክልላችንን ሁኔታ እንደዕድል በመጠቀም ወያኔ ለወታደራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶቹ መሳካት ሲል በትጥቅ፣ በገንዘብ፣ በፕሮፖጋንዳና የግንኙነት አመራር በመስጠት የሚደግፈው ሰርጎ ገብ ኃይል ስለመሆኑ እንዲታወቅልን እናሳስባለን” ሲል ገልጿል፡፡

“እነዚህ የህወሃትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት የወልቃይት-ጠገዴ አማራ ሕዝብን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ ሕዝቡ ወደ ዳግም ባርነት ላለመመለስ፤ የደም ዋጋ የከፈለበትን አስተዳደራዊ መዋቅሩን በመጠበቅ አማራዊ ነፃነቱን ለማስከበር ሲል ሰርጎ ገቦችንና ባንዳዎችን በይፋ ይታገላል” ሲልም አንስቷል፡፡

“መላ የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ የዞኑ አስተዳደርን ከህወሃት ሰርጎ ገቦችና ባንዳዎች ለመጠበቅ ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲሚወሰድ የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤቱ ወስኗል” በማለትም ህግ ማስከበር ወዳሉት እርምጃ እንደሚገቡ አስታውቀዋል እነኮለኔል ደመቀ ዘውዱ።

“በሌላ በኩል እጅግ ጥቂት የሚዲያ አካላት የወያኔን ተልዕኮ የወሰዱ ሰርጎ ገቦችን እንቅስቃሴ ከእውነታው ተቃራኒ በሆነ መንገድ መዘገባቸውን ተመልክተናል” ብሏል የዞኑ መግለጫ፡፡ 

ከሰሞኑ በወልቃይት ጠገዴ ዞን የአማራ ፋኖዎች በአገዛዙ ጦር ላይ እርምጃ ወሰዱ የሚሉ ዘገባዎች ተሰርተው ነበር፡፡ ተመልካቾቻችን በቀጣይ በጉዳዩ ላይ የሚኖሩ ግልጽ መረጃዎችን ወደ እናነት የምናደርስ ይሆናል፡፡

0 Comments

Login to join the discussion