የተዘጋጋው የአማራ ምድር

የአማራ ክልል ከተሞች በውጊያና በእንቅስቃሴ ገደብ እያሳለፉ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

ከነሃሴ 7 /2016 ጀምሮ የአማራ ፋኖ በጎጃም ፣ ካለፉት 2 ቀናት ጀምሮ ደግሞ የአማራ ፋኖ በወሎ እና የአማራ ፋኖ በጎንደር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እገዳና ልዩ ዘመቻ ማወጃቸው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም የአማራ ፋኖ ሸዋ ጥቅላይ ግዛት እዝ ዘመቻ እነዋሪን አስጀምሯል፡፡

ይህን የእንቅሳሴ እገዳና ልዩ ዘመቻ ተከትሎ የክልሉ መቀመጫ የሆነችውን ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል ፣ ከባባድ ውጊያዎች ተደርገዋል፤ ከአዲስ አበባ ባህርዳርና  ከአዲስ አበባ ደሴ የሚወስዱ ዋና መንገዶች መዘጋታቸውንም ሮሃ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

አለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ደግሞ በባሕር ዳር፣ ወልዲያ፣ ሸዋ ሮቢት እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ዛሬ ሰኞን ጨምሮ ባለፉት ቀናት ምን ሁኔታ ነበር የሚለውን ቃኝቷል፡፡ዘገባውም በከተሞቹ ውጊያና የእንቅስቃሴ እገዳ መኖሩን አመልክቷል፡፡ የብልጽግናው አገዛዝ ግን በከተሞች ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ቢጥርም አልተሳካለትም፡፡ 

የክልሉ ዋና መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር ከተማ አዲስ ውጥረት ከነገሰ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ከፋኖ መልዕክት በመተላለፉ የንግድ ተቋማት ተዘግተው የነበሩ ሲሆን፣ የመንግሥት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በፀጥታ ሥጋት ምክንያት ዝግ ሆነው እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ቢቢሲ አርብ ዕለት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ፣ ማንነታቸውን ከማያውቋቸው ሰዎች አምስት የሚደርሱ የጽሑፍ መልዕክቶች እንደደረሳቸው ተናግረዋል።የደረሳቸው መልዕክትም ‘ፋኖ አርብ 7፡00 ላይ ወደ ከተማዋ ሊገባ ስለሆነ፤ ቤታችሁ በመቀመጥ ትብብር እንድታደርጉልን፣ ካልሆነ ለሚደርስባችሁ አደጋ ኃላፊነቱን አንወስድም” የሚል ነው ይላሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ቅዳሜ እና እሑድ የተወሰነ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደነበር ገልጸው፣ እሑድ ከ7፡00 ሰዓት በኋላ ግን በከተማዋ ሦስት አቅጣጫዎች የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተናግረዋል።

በዘንዘልማ፣ በበላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ፣ እንዲሁም በሰባት አሚት ማረሚያ ቤት አቅጣጫ በከባድ መሣሪያ የታገዙ ውጊያዎች እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አባይ ማዶ አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ በዘንዘልማ አካባቢ ሲሰማ የነበረው ተኩስ እስከ ሌሊቱ 8፡00 ድረስ እንደነበርና በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ ያለው ደግሞ እስከ እሁድ ምሽት 3፡00 ድረስ መቆየቱን ተናግረዋል።

ሌላ ነዋሪም በበኩላቸው ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 13/2016  የንግድ ተቋማት እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት አልተመለሱም ብለዋል።

በከተማዋ ቀበሌ 11 አካባቢ ከፍተኛ ተኩስ እንደነበር የገለጹት ነዋሪው፣ “ውጥረቱ አሁንም እንዳለ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ የሰሜን ወሎ መቀመጫ በሆነችው ወልዲያ ከተማ ዛሬ ሰኞ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መቋረጣቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ ከወልዲያ ተነስተው ወደ ቆቦ፣ ወደ ደሴ እና ወደ ጎንደር መስመር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዛሬ ጠዋት ጀምሮ መቋረጡን ገልጸዋል።በክልሉ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማም ከዛሬ ሰኞ ጠዋት ጀምሮ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ እንዲሁም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጧል ብለዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ በከተማዋ ውስጥ አልፎ አልፎ ከሚታዩ ከባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ባጃጆች እና ከፈረስ ጋሪዎች በስተቀር የወትሮው እንቅስቃሴ የለም።

ይህ የሆነው “የፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በነሐሴ 13 እና 14/2016 ዓ.ም. ምንም ዓይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ትዕዛዝ አስተላልፏል” የሚል መረጃ ካሰራጨ በኋላ ነው፡፡

በምሥራቅ ጎጃሟ ደብረ ማርቆስም ከነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ሦስት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

0 Comments

Login to join the discussion