የእንቅስቃሴው መቋረጥና ዘመቻው

በአማራ ክልል አራቱም ክፍለ ግዛቶች የእንቅስቃሴ ገደቡ ቀጥሏል

የአማራ ፋኖ በጎጃምና የአማራ ፋኖ በወሎ በይፋዊ መግለጫ እንዲሁም የሸዋና የጎንደር አደረጃጀቶች ደግሞ በዘመቻ መምሪያ በኩል ያወጧቸው ትዕዛዛት እየተተገበሩ ይገኛሉ።

ሮሃ ሰሞኑን ባደረሰቻቸው ዘገባዎች በተለይም በጎጃምና በወሎ ክፍለ ግዛቶች የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወቃል።

ይህንኑ የአማራ ክልል ከተሞች የፋኖ መመሪያና የህዝቡ አተገባበር እንዲሁም የአገዛዙን የድንጋጤ እርምጃ አስመልክተው ገለልተኛ ሚዲያዎችም ዘገባዎችን እየሰሩ ይገኛሉ።

ዛሬ ጠዋት ዋዜማ በሰራችው ዘገባም የእንቅስቃሴ ገደቡን መቀጠልና የአገዛዙ ወታደሮችን እርምጃ ጠቁማለች።

በአማራ ክልል ከባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የጎጃም ዞኖች መንገዶች መዘጋታቸውን ዋዜማ ሰምቻለሁ ብላለች።

ይህን ተከትሎ በጎጃም በኩል ወደ ክልሉ ከአዲስ አበባ የሚገቡ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖችም ከቆሙ ሳምንት ተቆጥሯል።

በምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተቋረጠው፣ በፋኖ በኩል ላልተወሰነ ጊዜ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መሆኑንም ዘገባው ጠቅሷል።። 

  የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከቆመበት ጊዜ ወዲህ በጎጃም በሚገኙ አካባቢዎች፣ በአገዛዙ ወታደሮች እና በፋኖ መካከል የሚደረጉት ውጊያዎች እንደ አዲስ አገርሽተዋል ስትልም ዋዜማ ዘግባለች።  ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ኹሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች በምስራቅ ጎጃሟ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ መቆማቸውን ዘገባው አትቷል።

በፋኖና ህዝቡ መናበብ የደነገጡት የከተማዋ የትራፊክ ፖሊሶች እንቅስቃሴ ያቆሙ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ታርጋ ሲፈቱ እንደነበርም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሳምንቱን ከአዲስ አበባም ሆነ ወደሌሎች አካባቢዎች የሚደረገው እንቅስቃሴ መቆሙን ተከትሎ፣ የቤንዚን ዋጋ በመደበኛ ይሸጥበት ከነበረበት በሊትር 82 ብር ገደማ፣ ከሰሞኑ ወደ 150 ብር ከፍ ብሏልም ተብሏል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉትም በሸቀጦች ዋጋ ላይም ጭማሪ ታይቷል። 

  በጎንደር ከተማም እንዲሁ፣ ነዋሪዎቹ ከባድ ጦርነት ከተማዋ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውኛል ሲል ዘገባው ያክላል።

በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ያለፉትን ሁለት ቀናት ሥራ አቁመው መዋላቸውን ታውቋል።

ከጎንደር ወደ ባህር ዳር የሚደረግ ምንም ዓይነት የመኪና ጉዞ አለመኖሩንም ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።   

በተመሳሳይ ከትናንት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ የሚደረጉ ጉዞዎችም ተቋርጠዋል። ከደብረብርሃን ወደ ደሴ እንዲሁም ከደሴ ወደ ወልዲያ የሚሄዱ መኪኖች አለመኖራቸውን ዋዜማ አረጋግጣለች።

በአካባቢዎች የወረዳ ከተሞችን የሚያገናኙ መንገዶች ከትናንት ጀምሮ ብዙዎቹ ተዘግተዋል። 

በክልሉ የዞን ከተሞች በአገዛዙ ወታደሮች እጅ ቢሆኑም ከከተማ ወጣ ያሉ አካባቢዎች ደግሞ በፋኖ የተያዙ መሆናቸውንም የዋዜማ ዘገባ አልሸሸገም። 

በክልሉ ለ10 ወራት ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ካበቃ በኋላ ለተጨማሪ ወራት ባይራዘምም፣ በክልሉ አሁንም የምሽት ሰዓት ዕላፊ ገደብ አለመነሳቱን ዘገባው አስታውሷል። 

ሮሃ ባገኘቸው መረጃ ደግሞ የሰሞኑ የእንቅስቃሴ ገደብና የህዝቡ መመሪያውን መተግበር ያስደነገጣቸው የአገዛዙ ሹመኞች ወታደሮቻቸው በንፁሃን ላይ ግድያ በመፈፀም ህዝቡን እንዲያሸብሩና ፋኖን እንዳይቀበሉ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ባህርዳርን ጨምሮ በአገዛዙ ስር ናቸው በሚባሉ ዋና ዋና ከተሞች የፋኖ መመሪያ እየተተገበረ መሆኑን ተከትሎ አበባው ታደሰና አረጋ ከበደ ከዐቢይ አህመድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ይህንን አስመልክቶም ተላላኪዎች ሰሞኑን በተደጋጋሚ በስብሰባዎች ተወጥረዋል።

0 Comments

Login to join the discussion