የኢትዮጵያውያኑ ስቃይ በማይናማር

በማይናማር ለግርፋት ፣ ለጉልበት ብዝበዛና ለከፋ ስቃይ የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን “ድረሱልን” እያሉ ነው


ማይናማር ገብተው መውጫ ያጡ 700 ኢትዮጵያውያን በቻይናውያን በሚመራ አንድ አደገኛ አለም አቀፍ የአጭበርባሪ ድርጅት ውስጥ በግድ ሰራተኛ መደረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በማይናማር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግርፋት እና በግዴታ የሚደረግ የጉልበት ብዝበዛ እየተፈፀመባቸው መሆኑም ሰሞንኛ መነጋገሪያ ጉዳይ ነው፡፡

ካለ ክፍያ በቀን ከ17 ሰዓት በላይ እንደሚሰሩ፣ አሁን ላይ ሳሙና መግዣ እንኳን እንደሌላቸውም ኢትዮጵያውያኑ ይናገራሉ፡፡

እነዚህ ዜጎች በቻይናውያን በሚመራ አንድ አደገኛ አለም አቀፍ የአጭበርባሪ ድርጅት ውስጥ በግድ ሰራተኛ መደረጋቸውን ለማወቅ ችያለሁ ሲል የዘገበው ደግሞ መሰረት ሚድያ ነው። 

እነዚህ ከ1,000 እስከ 1,500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን በታይላንድ እና ማይናማር አጎራባች አካባቢ እንደሚገኙ ጠቅሰው ኮምፒውተር ላይ ታይፕ የማድረግ ስራ አለ ተብለው ተታለው ወደ ስፍራው እንደተወሰዱ ይጠቅሳሉ። 

ሚድያው በድብቅ ስልኮች ማውራት የቻሉ አራት ኢትዮጵያውያንን ላለፉት ሶስት ቀናት ሲያነጋግር መቆየቱን ገልጿል። 

እነዚህ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ዜጎች ስራቸውን በተመለከተ "በደላሎች ተታለን ታይላንድ ስራ አለ ብለውን ነው ወደ ታይላንድ የወሰዱን። ከዛም 11 ሰአት በመኪና ከተጓዝን በኋላ በታይላንድ ድምበር አርገው ማይናማር ውስጥ ለሚገኝ የቻይና የማጭበርበር ድርጅት ሸጡን።" ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

"እዚህ ያለነው ከ600-700 ኢትዮጵያውያን ነን። በየቀኑ በዱላ ድብደባ ይደርስብናል፣ በኤሌክትሪክ ሾክ ያረጉናል፣ ጨለማ ክፍል ይጥሉናል፣ ለቀናት በአሰቃቂ ሁኔታ መታሰር፣ ከባድ ስፖርት መስራት፣ ለሰው ልጅ ከባድ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ይህን መረጃ እራሱ ዶርም ውስጥ ተደብቄ ነዉ የምሰጥህ። ዙርያው በታጠቀ ፖሊስ ስለሚጠበቅ መውጣት አንችልም።" ሲሉም ስለሚደርስባቸው ግፍ ያነሳሉ፡፡

"የተለያዩ ሰዎች ጋር  እንደ ዋትሳፕ ባሉ መነጋገሪያዎች በፅሁፍ ማነጋገር ነው፣ ስናነጋግር ሴት መስለን ነው የምናወራቸው፣ አካውንቱን ራሳቸው ቻይናዎቹ ይከፍቱልናል። እንደ ኢራቅ፣ ቱርክ፣ ሩስያ፣ ካዛክስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ አዘርባጃን እና አርሜንያ ያሉ ሰዎችን ነው እንድናጭበረብር የሚያስደርጉን" ይላሉ፡፡

"ለምሳሌ ሴት መስለን አገራቸውን መጎብኘት እንደምንፈልግ እንነግራቸዋለን፣ ያው ወንዶች ናቸው። በቀጣይ ወር ስለምመጣ ጓደኛዬ ሁን ብለን እናወራለን፣ ከዛም ቀስ ብለን በተለያዩ ዘዴዎች ገንዘብ እንቀበላለን። በዚህ አይነት ቻይናዎቹ ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ዶላር ሊያገኙ ይችላሉ።" በማለትም የስራውን ባህሪ ያስረዳሉ፡፡ 

“በጉግል መተርጎምያ እያረግን ነው የምናወራቸው፣ ሙሉ በመሉ በፅሁፍ ነው። ተጠራጥረው እናውራ ካሉ ግን ለዚህ ተብላ የተዘጋጀች ሴት ቻይናዊት አለች።" ሲሉም ያክላሉ፡፡

"ስራው የእድል ነው” የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ  “ቻይናዎቹ ታርጌት ይሰጡናል፣ እሱን ካላመጣን በቃ ስቃይ ነዉ። በአንድ ትንሽ ግቢ ውስጥ ብዙ company አለ፣ አንድ company ማለት አንድ ክፍል ነው፣ የየራሱ ታርጌት አለው። አሁን እኔ ያለሁበት company 15,000 dollar ከአንድ ሰው በወር ይጠብቃል። ይህ ካልሆነ ድብደባ ይፈፀምብናል። ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህን ማድረግ አይችልም።"

"እዚህ ግቢ የህንድ እና የስሪላንካ ዜጎች ነበሩ” ያሉም ሲሆን እነሱን አሁን መንግስታቸው አውጥቷቸዋል። ስለዚህ እኛ ላይ በርትተዋል።" ሲሉም የሚደርስላቸው መንግስት እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ስለምግብና ክፍያ ሲጠየቁም "ምግብ የእነሱ አገር ስለሆነ ለእኛ ከባድ ነው፣ ግን እሱም በቂ አይደለም። መተኛት የምንችለው ለ 3 ሰአት ተኩል ብቻ ነው። ብር የሚባል ነገር አይተን አናውቅም፣ ክፍያውን የሚወስዱት ቻይናውያኑ ናቸው። የሆነ ሰሞን ትንሽ ያገኙ ልጆች ነበሩ፣ ግን ቅጣት ብለው መልሰው ወሰዱባቸው።" ይላሉ፡፡

ዜጎቹን አገር አልባ ያደረገው የብልጽግናው አገዛዝ በዚህ መልኩ ተታለው ስቃይ ስለሚደርስባቸው ኢትዮጵያውያን ግድ እንደማይሰጠው ይታወቃል፡፡ በዚህም ዐቢይ ስልጣናቸውን ለማጽናት በሚሮጡበት ወቅት የተጣሉ ሁለት የአረብ አገር ሴቶችን ሲያስታርቁ እንዳልነበር አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ግልጽ የወጣ ግፍና ባርነት ውስጥ ሲወድቁ ዞረው ማየት አልፈለጉም፡፡

ምክንያቱም በአገር ውስጥ ያለውንም ህዝብ በኑሮ ውድነት ፣ በጦርነት ፣ በማፈናቀል እየቆሉት ያሉት ራሳቸው ናቸውና፡፡

0 Comments

Login to join the discussion