የአገዛዙ ጦር አደገኛ ውሳኔ

በሶማሊያ የሚገኘው የአገዛዙ ጦር የሶማሊያን አየር ማረፊያዎች በመቆጣጠር ወረራ መጀመሩ ተነገረ

ብርሃኑ ጁላ የሚመሩት የአገዛዙ ጦር በትላንትናው እለት የሶማሊያ ቁልፍ የአየር ማረፊያዎች መውረሩ ተነግሯል።
ይህ  ጦር ተቆጣጥሯቸዋል የተባሉት የአየር ማረፊያዎች የጌዶ ፣ የሉቅ ፣ የዶሎውና የባርደሬ አየር ማረፊያዎችን ነው፡፡
ይህም የተደረገው የሶማሊያ ጦርም ሆነ በቦታው ለመስፈር እየተዘጋጀ የነበረውን የግብፅ ጦር የትም መንቀሳቀስ እንዳይችል ለመቁረጥ በሚል ነው፡፡
ሶማሊያ ከነዚህ አራቱ ክልሎቿ ጋር የሚያገናኟት አየር ማረፊያዎች እነዚህ የነበሩ ሲሆን በሞቃዲሾና በአየር ማረፊያው መካከል ያለው ግዛት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር የሚገኝ በመሆኑ የሶማሊያ እንቅስቃሴዎች በክልሎቹ እንዲቋረጥ የሚያደርግ ነው የሚል መረጃ ነው ጋርዌ ኦንላይን በተባለው ሚዲያ የተሰራጨው፡፡
ይህን መረጃም በአገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እያጋሩት ነው፡፡
ግብፅ ወደ ሶማሊያ 5,000 ወታደሮቿን ያስገባች ቢሆን ኢትዮጵያ የሶማሊያን አየር ማረፊያዎች መቆጣጠሯን ተከትሎ የግብፅን ወታደሮች እንቅስቃሴ ለመገደብ ያለመ ነው ተብሏል ይህ ወረራ፡፡
እንግዲህ ይህን ወረራና ትንኮሳ የፈጸመው ደግሞ ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብና በአፍሪካ ህብረት ይሁንታ ወደ ቀጠናው ልካው የነበረው የሰላም አስከባሪ ጦር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለለፉት ሃምሳ አመታት በአፍሪካና ከአፍሪካ ውጪ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወስዳ ስታስፈጽም እንዲህ አይነት አሳፋሪና የገባችባቸውን ሃገራት የመውረር ተግባር ፈጽማ አታውቅም፡፡
የአብይ አህመድ አሊ አገዛዝ ግን በዲፕሎማሲም ሆነ በአገር ውስጥ አስተዳደር የከሸፈ በመሆኑ ለእንደዚህ አይነት ስስ አለማቀፋዊ ጉዳዮች የሚጨነቅ አይደለም፡፡
በመሆኑም በአገር ውስጥ ጦርነት ላይ የሚገኘው አገዛዝ በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ ሌላ ቀጠናዊ ጦርነት በይፋ የሚያስጀምረውን ውሳኔ ወስኗል፡፡
ይህም ሶማሊያ ከግብጽ ጋር የጀመረችውን ትብብር አስቀጥላ ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ብትሰነዝርና ጦርነቱ በይፋ ቢጀመር ፣ የደሃ ኢትዮጵያውያን ልጆችን የጥይት ራት ለማድረግ መዘጋጀቱን ያመላከተበት ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የብልጽግና ትንኮሳና የወረራ እቅድ የሚቃወሙና አካሄዱን ባለመደገፍ የቆሙ አካላትን “ሉዓላዊነታቸው ሲደፈር ዝም የሚሉ” በሚል ለማሸማቀቅ የሚሯሯጡ ተከፋይ የብልጽግና አክቲቪስቶች በየመንደሩ እየታዩ ነው፡፡

0 Comments

Login to join the discussion