የአርበኛ ዘመነ ካሴ መልዕክት
አርበኛ ዘመነ ካሴ በቅርቡ የብልጽግናው አገዛዝ ማስቆም የማይችለው ግዙፍ አዲስ ዘመቻ እንደሚጀምሩ አሳወቀ
የአማራ ፋኖ በጎጃም ዋና ሰብሳቢ አርበኛ ዘመነ ካሴ ዛሬ ጥቅምት 8/2017 ዓ/ም ለአማራ ህዝብ እና ለክፍለ-ዘመኑ የአፍሪካ ቀንድ ክስተት የአማራ ፋኖ አመራር እና አባላት ፣ ለአማራ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ፣ ለአማራ ዲያስፖራ እንዲሁም ለሆድ አደር ባንዳዎች መልዕክት አስተላልፏል፡፡
አርበኛው በመልዕክቱ “በዘመቻ መቶ ተራሮች ባለፉት አስራ ስድስት ቀናት እጅግ የበዙ የድል ታምራትን አሳይተናል” ያለ ሲሆን “በሌላ ድንቅ የዘመቻ እቅድ እስኪተካም ዘመቻ መቶ ተራሮች ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።
“ይህ የህልውና ትግል በፍጥረቱም፥ በፍጥነቱም በባለቤቶችም ብዙ ነገሩ የተለዬ በመሆኑና በሌሎች ብዙ አካባቢያዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ምክንያት አውቆ የተኛ የሚመስለው አለምም ሲያንቀላፋ አንኳን አንድ አይኑን ከፍቶ ያለመዘናጋት የሚከታተለው ትግል ነው ስለዚህ እንበርታ” ሲል አብራርቷል።
አርበኛ ዘመነ “ሃገር ሽጠው በሚያገኙት የደም ገንዘብ አሮጌ ተራ ወርደው በሚሸምቱት ድሮንና ተተኳሽ አይደለም ከዋክብት ቦንብ ሆነው የአማራ ህዝብ ላይ ቢዘንቡ እንኳን ጠላቶቻችን ይህን ትግል ማሸነፍ አይችሉም” ሲል አረጋግጧል።
“እምቢ ያለን ህዝብ፥ ለህልናው ላለመጥፋት የሚታገልን ህዝብ ማሸነፍ ፈፅሞ አይቻልም” የሚለው ዋና ሰብሳቢው “ከምድረገፅ ላለምጥፋት መሳሪያ ያነሳን ህዝብ ከማሸነፍ የፀሀይን ከምስራቅ ወደ ምእራብ ተፈጥሯዊ የጉዞ ኡደት ከሰሜን ወደ ደቡብ ማዞር ይቀላል” ሲልም አክሏል።
“ከፈጣሪ በታች ትልቁ ጉልበት ያለው የአመፀ ህዝብ መዳፍ ላይ ነው። እንበረታ እንፅና” ይላል፡፡
ዘመነ ለአማራ ህዝብ ባስተላለፈው መልዕክቱም “ጠላት ከምድረ ገፅ ሊፍቅህ በሰማይም በምድርም ጭፍጨፋ እየፈፀመብህ ቢሆንም ከታሪክህ ፣ከማንነትህና ከውብ እሴቶችህ አኳያ ይህን ዘመን በድልና በኩራት እንደምታልፈው የደቂቃ ጆሮ ካዋስከው ተራራውና ሸለቆው በደምህ ደረቱ ላይ ከመዘገበው ወፍራም ታሪክህ ብዙ አብነቶችን መዞ ይነግርሃል” ብሏል።
የአማራ ህዝብ በመካከለኛው ዘመን ለ15 ዓመታት ያደረገውን ተጋድሎና በጣሊያን ጊዜ ለ5 ዓመታት ያሳለፈውን የአርበኝነትና የአሸናፊነት ታሪክም አውስቷል፡፡
ለፋኖ አመራርና አባላት ባስተላለፈው መልዕክቱም “ታሪክ እየሰራን መጥተናል። በቅርቡ በዘመቻ መቶ ተራሮች ተአምር አሳይተናል፥ የጠላትን አንገት ዳግም ቀና ብሎ እንዳያይ አድርገን ወደ ግራ ሰብረናል። ከምናውቅበትና ከመጣንበት መደበኛው ፋኖአዊ ውጊያችን ባለፈም ጠላት ኪሊማንጃሮን ነቅሎ አምጥቶ ምሸግ ቢገነባ እንኳን ማስቆም የማይችለው አንድ ሌላ ድንቅ ዘመቻ በቅርቡ ይኖረናል። እንበርታ! እንፅና!!፥ፅናት የትግላችን ደም ስር የድላችን ምሰሶ ነው” ሲል ሌላ አዲስ ዘመቻ እንደሚኖራቸው አሳውቋል።
ለአማራ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች በተላለፈው መልዕክትም “ከሰሞኑ የጀመራችሁት የተናበበ እና የተቀናጀ የስርአቱን ግፎች የማጋለጥ ዘመቻ እዚህ መሬት ላይ ያለን ወንድምና እህቶቻችን በእጅጉ አስደስቷል። አኩርቷል” ሲል አመስግኗል።
በዚህ ጅምራችሁም ግፉበት ሲል አሳስቧል፡፡
ለአማራ ዲያስፖራዎች ባስተላለፈው መልዕክትም “ከሰሞኑ ጥሩ መነቃቃት እያየን ነው። ጥሩ ነው። በእጅጉ ግን ይቀራል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
“እናቶቻችሁ ከነ ከብቶቻቸው በድሮን በሚጨፈጨፉበት ዘመን ለሰበብ የሚሆን የሚያደናቅፍ የእናት መቀነት የለምና ጥሪያችንን ሰምታችሁ ውጡ!!በሁሉም ዘርፍ ውጡና ታገሉ። ያበቀለው መሬት በእሳት እየተጠበሰ የሌላ ሃገር መሬት ላይ ችሎ እንቅልፍ የሚተኛ ጤነኛ አማራ ካለ የኛ አይደለም” ብሏል።
“ከነ ጃሪና ኮሎ ጋር አብራ ለምትገደል እናት ሰልፍ መውጣት ያን ያክል ከባድ ነው?” ሲል የሚጠይቀው ዘመነ “አይምስለኝም” ሲል መልሷል።
ለአገዛዙ አድረው በአገዛዙ ካምፕ ላሉ አማራዎች ባስተላለፈው ጥሪም “በተለያዬ ጊዜ ያደረግነውን ጥሪ ተቀብለው የተቀላቀሉን መሰሎቻችሁ ከህሌናም፥ ከታሪክም ተጠያቂነት ራሳቸውን አድነው ከሰቀቀን ወጠው ሂወታቸውን እንደ አዲስ መኖር ጀምረዋል” ሲል አሳውቋል።
“እነ አብይ ዛሬ ይንቋችኋል፣ ይጠሏችኋል ፣ ነገ አውጥተው ጎዳና ላይ ይጥሏችኋል። ጎዳና ላይ የውሻ ሞት ትሞቱና ያሳደጋችሁ ምድር ተከፍቶ ይውጣችኋል። ስለዚህ ያ ከመሆኑ በፊት ኑ” ብሏል መልዕክቱን ሲያሳርግ፡፡
Login to join the discussion