የአርበኛ አስረስ ማብራሪያ
የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የሻለቃ አመራር የፋኖ አባላት እንዳሉ የአማራ ፋኖ በጎጃም አሳወቀ
የአገዛዙ የመከላከያ ጀነራሎች በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት ከትግራዩ ጦርነት በባሰ መልኩ መክሰራቸውን እና መጎዳታቸውን መገምገማቸው ተነግሯል፡፡
እንዲሁም ከፋኖ ጋር እያደረጉት ያለው ውጊያ በደንብ ያላቀዱበትና በስሜት የገቡበት እንደሆነም በግምገማቸው ማንሳታቸው ተሰምቷል፡፡
ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ለአንከር ሚዲያ ማብራሪያ የሰጠው የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አስረስ ማረ “ ወደ አማራ ክልል ከገባው የመከላከያ ጦር ውስጥ የሚተርፍ የለም” ብሏል፡፡
ብልጽግና በዚህ መታበዩ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ አገሪቱ ላይ መከላከያ ሰራዊት የሚባል አይኖርም ሲል ፋኖ አስረስ ገልጿል፡፡
እንዲሁም ዐቢይ አህመድ በትግራዩ ጦርነት ትንሽም ቢሆን ለፕሮፓጋንዳ የሚመቸው ጉዳይ ነበረው ያለው አርበኛው በአማራ ክልሉ ጦርነት ግን ወታደሩንም ሆነ ህዝቡን የሚቀሰቅስበት ምክንያት የለውም ሲል አብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል የብልጽግና ተላላኪና ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት እንደነ ዶክተር ገመቺስ አይነት ፓስተሮች ከሰሜን የሚመጣው ሃይል ሃይማኖትህን ሊያጠፋ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ ጀምረዋል በሚል ከሚዲያው ለተነሳለት ጥያቄም ፋኖ አስረስ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በምላሹም የኦርቶዶክስ ፣ የፕሮቴስታንትና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በትግላችን ውስጥ አሉ ብሏል፡፡እንዲሁም የኦሮሞ ወጣቶች ናቸው በጦርነቱ እያለቁ ያሉት በሚል ከኦሮሚያ ክልል ለሚነሱ ጥያቄዎች አርበኛው በሰጠው ምላሽ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን የኦሮሞ ወጣት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል፡፡
ለአብይ ስልጣን ሲባል የኦሮሞ ወጣት ማለቅ የለበትም ሲል ያከለው ምክትል ሰብሳቢው አብይ የሚያበለጽገውና የሚጠብቀው የኦሮሞን ህዝብ ሳይሆን ስልጣኑን ነው ሲል ገልጿል፡፡
አክሎም በፋኖ ትግል ውስጥ እስከ ሻለቃ አመራርነት የደረሱ የኦሮሞ ተወላጅ ፋኖዎች አሉ ሲል ተናግሯል፡፡
የአማራን ህዝብ በድሮን ጥቃት እየጨፈጨፈ ያለው የብልጽግና ሃይል በህዝቡ ላይ ለመሳለቅ በሚመስል መልኩ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ሊያካሂድ ማሰቡም ተነግሯል፡፡
አርበኛ አስረስ በበኩሉ “ በድሮን ፣ በታንክ ፣ በስናይበር ፣ በዙ ፣ በድሽቃ ፣ በሞርታር ፣ በጠመንጃ ፣ በጀት ያላስቆመውን የአማራ ትግል በሰልፍ ሊያስቆመው አይችልም ብሏል፡፡
የብልጽግናው ስርዓት ሙሉ በሙሉ በክልሉ ፈርሷል ፣ መልሶ እግሩን ሊተክል አይችልም ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል አመራሩ፡፡
Login to join the discussion