የጀነራሎቹ ፕርፓጋንዳና ደብረማርቆስ
የብልጽግና ጀነራሎች እያካሄዱት ባለው የአማራ ክልል ስብሰባ “ፋኖን አጥፍተነዋል” የሚል ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ነው
የዋሺንግተን ግዛት የተወሰኑ የብሔራዊ ጥበቃ አባላቱ በተጠንቀቅ እንዲሆኑ ማዘዙን አስታወቀ
የብልጽግና የጦር አዛዦችና ካቢኔዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ስብሰባ ማካሄዳቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ በደሴና በኮምቦልቻ ጀነራል በላይ ስዩም በደብረማርቆስ ጀነራል መሃመድ ተሰማ የመሯቸው ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡
በደሴና በኮምቦልቻው ስብሰባ የተገኙት ጀነራል በላይ ስዩም ለአመራሩ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ ይህም መመሪያ ፋኖ መጥፋት አለበት ለዚህም ህዝቡ ይተባበር የሚል ሲሆን ዛቻ የተቀላቀለበት እንደነበርም ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረማርቆስ ጀነራል መሃመድ ተሰማ የዛሬ ዓመት ጥቅምት ወር ገደማ የተናገረውን ንግግር በዛው ከተማ ደግሞታል፡፡
ጀነራሉ “ፋኖን አጥፍተናል ፣ በትነነዋል ፣ አዳክመነዋል ፣ከፍተኛ ውጊያ አያካሄድን ነው፣ በአየር ሃይል ጥቃት እየፈጸምን ነው” ሲል ነው የተሰማው፡፡ ይህን የሰሙት ተስብሳቢዎች አብዛኛዎቹ የብልጽግና ካድሬዎች ስለሆኑ የዛሬ ዓመትም እኮ እንዲህ ተብለን ነበር አላሉም፡፡
ይሁን እንጂ መሃመድ ተሰማ የዛሬ ዓመትም በተመሳሳይ በደብረማርቆስ ፋኖን አጥፍተነዋል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ጀነራሎቹ ይህን ቢሉም የአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢ በፋኖ ቁጥጥር ስር መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የብልጽግናው ሃይል አዲስ የውጊያ ዘመቻ ይዞ የመጣ ሲሆን ይህ ስልትም የክላስተር / የኩታ ገጠም/ ዘመቻ ለማድረግ መወሰኑ ነው የተሰማው፡፡
በዚህ በኩታ ገጠም ውጊያ አንድን ዞን ከሌላ ዞን ጋር የሚያዋስነውን ቦታ በመናበብ ውጊያውን እንዲመሩና የመረጃ ልውውጥ እያደረጉ እንዲዋጉ የሚል ነው፡፡
ብልጽግና ከፋኖ ጋር እያካሄደ ባለው ውጊያ ያልተገበረው የዘመቻ አይነትና ያልቆረጠው የመጨረሻ ዘመቻ የለም ፣ ይሁን እንጂ ሁሉም ዘምቻና እቅዶች ፋኖን የበለጠ እያስታጠቁትና እያደራጁት አልፈዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ዐቢይ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ያደረጓቸው ለገሰ ቱሉ በእነ ዳንኤል ክብረት የተደረሰውን አዲስ የፕሮፓጋንዳ ስልት ተቀላቅለዋል፡፡
እኒህ ጥላቻና ፍረጃን በመቀስቀስ የሚታወቁት የብልጽግናው ሹም በስተርጅና እድሜያቸው ለብልጽግና በሆዳቸው አድረው በአማራ ህዝብ ላይ ጦር ካወጁት መካከል ናቸው፡፡
በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ፅንፈኛው ቡድን በምንም መመዘኛ ቢለካ ለአማራ ህዝብ ጥቅም የሚሆን አንግቦ የተነሳው ዓላማም ሆነ ዕቅድ የለውም” ሲሉ ለአማራ ከፋኖ ይልቅ ዐቢይና ሽመልስ አብዲሳ ይጨነቁለታል ብለዋል።
ፋኖ የሆነው ራሱ የአማራ ህዝብ መሆኑ ቢታወቅም ፣ የተሰቃየውና ግፍ የተፈጸመበት ራሱ አማራ መሆኑ ሃቅ ቢሆንም እነ ለገሰ ቱሉ ግን ይህን ሃቅ መካድ ዋነኛ ስራቸው ነው፡፡
ክልሉን በድሮን ፣ በከባድ መሳሪያ ፣ በሄሊኮፕተር እያወደመ ያለውን የብልጽግና ስብስብ በሚኒስትርነት የሚያገለግሉት እኒህ ሰው ፋኖን ክልሉን በማውደም ሲከሱት ተስተውለዋል፡፡
ፋኖ የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ገፍቶ ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ አርሶ አደሩን ሰብል እንዳይሰበሰብ፣ ነጋዴውም ተሯሩጦ እንዳይሰራ እያደረገ ነው” ሲሉም ሰሞንኛውን የመንግስታቸውን ፕሮፓጋንዳ ነዝተዋል፡፡
ይህም የገበሬ ቤቶችን እና ትምህርት ቤቶችን በከባድ መሳሪያና በድሮን እየደበደበ ክልሉን ማውደሙን “የአባብዬን እከክ ለማምዬ ልክክ” አይነት ተረት ለማምጣት ፈልጎ ነው፡፡
በሌላ በኩል በራያ አላማጣና ዋጃ አካባቢዎች የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ አባላትና አቀንቃኞች በገፍ እየታሰሩ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ወጣቶቹ ለመታሰራቸው የሚቀርብላቸው ምክንያት ፋኖ ናችሁ የሚል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ወጣቶቹ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ በመሆን በአካባቢው ተቋቁሞ በነበረው የአማራ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የእስሩን ጥቆማ ለአገዛዙ መከላከያ የሚሰጡት የህወሃት ታጣቂዎች ሲሆኑ ፣ ህወሃት አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመውሰድ እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ነው እያሳሰረ ያለው ተብሏል፡፡
በፍኖተ ሰላም ትናንት ከሰዓት በኋላ ሆዳሽ በተባለ ቦታ ውጊያ ሲካሄድ ፣ ሃናማሪያምና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡
በደብረማርቆስ የአገዛዙ ጦር የዮፍታሄ ንጉሴ ክፍለጦር የተክለሃይማኖት ብርጌድ ፋኖዎችን ለማፈን ሲንቀሳቀሱ ፋኖዎቹ በበኩላቸው ወደ ከተማዋ በመጠጋት በከተማዋ ዙሪያ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ውጊያ ሲያካሂዱ ውለዋል፡፡ ይህ ውጊያ እየተካሄደ ያለውም እነ ማሃመድ ተሰማ በከተማዋ ስብሰባ እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው፡፡
Login to join the discussion