የአቸፈሩ ጭፍጨፋና የቢቢሲ ዘገባ
በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ አጋለጠ
በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ በብልጽግናው አገዛዝ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ህጻናትን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጥቃቱ ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ከወረዳው ዋና ከተማ ዱርቤቴ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አርጌ በተባለች ታዳጊ ከተማ ላይበተከታታይ ሦስት ጊዜ መፈጸሙን እማኞች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሮሃም በወቅቱ ነዋሪዎችንና የፋኖ ሃይሎችን አናግራ ይህ ጭፍጨፋ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
ጠዋት 1፡10 አካባቢ በከተማዋ ገበያ አካባቢ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ ጥቃቱ እንደተፈጸመ እማኝነታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ “ከልጅ እስከ አዋቂ ያለቀበት” ነው ብለውታል።
በድሮን ጥቃቱ መረብ ኳስ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች፣ ለሽምግልና የተቀመጡ ሰዎች፣ ህክምና ላይ የነበሩ እናቶች፣ የጉልበት ሠራተኞች፣ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እና እርሻ ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች ሰለባ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሦስቱም አካባቢዎች በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎች የጠቆሙ ሲሆን፤ ቢቢሲ አካባቢዎቹ ከ300 ሜትር ራዲዬስ ባነሰ ርቀት እንደሚገኙ በካርታ እና በሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።
ከጥቃቱ አንድ ቀን አስቀድሞ የድሮን ቅኝት እንደነበረ ለማመልከት “አየሯ ስትዞር ነበር” ያሉት ነዋሪዎች ጥቃቱን “ከተማዋን በሙሉ ለማጥፋት” ይመስል ነበር ብለውታል።
“ህጻናት የለ፣ ሽማግሌ የለ፣ ወጣት የለ በሙሉ መደዳውን [ተመተዋል]። ጥግ ለጥግ የነበሩ ብዙ ቤቶችም ተመተዋል” ሲሉ የጥቃቱን መጠን የገለጹ አንድ የዓይን እማኝ፤ ንጹሃን ናቸው ሲሉ ስለ ሟቾቹ ማንነት ተናግረዋል።
“የእግዜር ቁጣ ነው የመሰለን፤ ከሰማይ መጥቶ ነው እንደ መብረቅ የወደቀብን” ያሉ አንድ ነዋሪ ያልጠበቁት ክስተት መሆኑን መስክረዋል።
የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው አካባቢው ላይ በፍጥነት እንደደረሱ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ በየቦታው የወዳደቀ አስከሬን ማየታቸውን ጠቁመው ሁኔታውን “ዘግናኝ” ሲሉ ገልጸውታል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ቤተ ክርስቲያን እንደነበሩ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ በቅጽበቱ ራሳቸውን ለመከላከል “በያለንበት ተኛን” ብለዋል። እርሳቸው እና አብረዋቸው የነበሩ ስድስት ሰዎች “በቸርነቱ” ቢተርፉም አቅራቢያቸው የነበሩ ሰባት ሰዎች ግን እንደተገደሉ ተናግረዋል።
“ሰው መሆን ያስጠላል። ሰው በሰው ላይ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ሲፈጽም አይቼ አላውቅም” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት የሚገልጹት ነዋሪው፤ “ከባድ፤ አስከፊ ጥቃት ነው የደረሰው” ብለዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ ኳስ ጨዋታ ላይ የነበሩት ከ13 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ነፍሰ
ጡር እናቶች የጥቃቱ አስከፊነት መገለጫ ናቸው ብለዋል።
ጤና ጣቢያው ላይ በደረሰው ጥቃት የእርግዝና ክትትል እና ምጥ ላይ የነበሩ እናቶች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህን የረጋገጡት እና ጥቃቱ ሲደርስ ጤና ጣቢያው ውስጥ የነበሩ አንድ ባለሙያ፤ የእናቶች ክትትል ማዕከል ላይ የደረሰው ጉዳቱ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፤ አምስት ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሌሎች ሁለት አስታማሚዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“ውስጥ የተኙ እናቶች ላይ ነው የወደቀው” ያሉት የጤና ጣቢያው ባለሙያ በጥቃቱ ሦስት ሴት የጤና ባለሙያዎች ላይም የመቁሰል ጉዳት መድረሱን አመልክተው፤ የደረሰውን ጉዳት “መሪር” ሲሉ ገልጸውታል።
ሦስት እናቶችም “በድንጋጤ” ጽንሳቸው እንደወረደባቸው ባለሙያው ተናግረዋል።
ገበያው አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ቤታቸው ውስጥ ቁርስ እየበሉ ነበር የተባሉ አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላትም ነፍሰ ጡር እናት እና አባት ከሦስት ልጆቻቸው ጋር መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሟቾቹ ጎረቤት የሆኑ አንድ ነዋሪ “አንድ ላይ ነው የረገፉት” ብለዋል። የልጆቹ እድሜ ከ10 ዓመት እስከ 17 ዓመት እንደሚደርስ የገመቱት ጎረቤት፤ ነፍሰ ጡር የነበረችው እናት “እግዜር የሰጣትን ሳታራግፈው መሄዷ...” በነዋሪው ዘንድ ድርብርብ ሐዘን መፍጠሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ ሰባቱ ዘመዶቻቸው እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “ከአንድ ቤት እስከ አምስት ቤተሰብ የሞተ አለ” ሲሉ እልቂቱን ገልጸዋል።
የ15 ዓመት ቅርብ ዘመዳቸው በዚህ ጥቃት እንደተገደለ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ “ሐዘኑ ያልገባበት ቤት የለም” ሲሉ ከአንድ ቤተሰብ ሁለት እና ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“እልቂት ነው” ሲሉ ክስተቱን የገለጹ ሌላ ነዋሪ፤ “ይህን ያህል ስንኖር እንዲህ ዓይነት ነገር ማየት ቀርቶ ሰምተን አናውቅም። በንጹሃን ላይ እንዲህ ያለ አደጋ መድረሱ ከባድ ነው” ብለዋል።
አንድ አስከሬን ያነሱ ነዋሪም ባዩነት ነገር መረበሻቸውን ገልጸው “አሞኛል” ብለዋል።
ሌላ ነዋሪም “ያን ሁሉ ያየ እንጀራ የሚበላ እኮ የለም። ትናንትናም ዛሬም የሚበላ የለም” ሲሉ እንዲሁ መረበሻቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ሰውነታቸው ተለያይቶ እና ፊታቸውን መለየት ተቸግረው እንደነበር የተናገሩት ነዋሪው፤ የድሮን ቅኝት በመቀጠሉ በስጋት በጅምላ ለመቅበር መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የእገሌ ወንድም፣ የእገሌ እህት፣ የእገሌ ልጅ፣ የእገሌ አባት እየተባለ እንጂ መልኩ አይታወቅም” ሲሉ አስከሬን ለመለየት መቸገራቸውን ገልጸው፤ በአንድ መቃብር እስከ 15 ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን ተናግረዋል።
“[አስከሬን] እየተለቃቀመ በጋሪ ነው የተጫነው። ተሰባስቦ ነው የተቀበረው” ያሉት ነዋሪዎች ቀብር በቅርብ ርቀት በሚገኘው እና በጥቃቱ አነስተኛ ጉዳት ደርሶበታል በተባለው ዝብስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን “ፍትሃት” ሳይደረግ
አስከሬን ያነሱ አንድ ነዋሪ ጥቃቱ በደረሰበት ቀን 44 አስከሬን ማግኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ በማግስቱ ደግሞ የአራት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል።
ሌሎች ሁለት ነዋሪዎች ደግሞ በጥቃቱ የተገደሉ “43 ሰዎችን” መቁጠራቸውን ገልጸው፤ 21 ሰዎች ደግሞ ቁስለዋል ብለዋል።
በድሮን ጥቃቱ 64 ሰዎች መጎዳታቸውን የተናገሩት የጤና ጣቢያው ባለሙያ፤ 43 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ ጭፍጨፋ የተፈጸመው ፋኖ ጨርሶ በአካባቢው በሌለበት ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ “ ይህ ለምን እንደሆነብን አልገባንም” ብለዋል፡፡
አሁን ላይም ህዝቡ ከተማና መንደሩን ጥሎ እየሸሸ ፣ ህጻናት በጭንቀት በጸበልና በህክምና ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
Login to join the discussion